የኢፌዴሪ ቀዳማዊት እመቤት የጽህፈት ቤታቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ አደረጉ

100
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 የኢፌዴሪ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው የጽህፈት ቤታቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ አድርገዋል። ቀዳማዊት እመቤቷ በተለይም በህጻናትና በሴቶች ደህንነት ትኩረት በማድረግ በህጻናት ላይ የሚታየውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲሁም ያለእድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ ተገዶ መደፈርና የሴት ልጅ ግርዛትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለመከላከል እንደሚሰሩ ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል። ትምህርት ድህነትን ለመዋጋት ወሳኝ ቁልፍ መሆኑን በእጅጉ የሚረዱት ቀዳማዊት እመቤቷ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ሁሉ መማር እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርጉም ነው በመግለጫው የተመለከተው። ለትምህርት ማነቆ  የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ  በተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሳቢያ በየጎዳናው ያሉ ህጻናትና አረጋውያን መጠለያ፣ ምግብና እንዲሁም አስፈላጊውን የጤና እንክብካቤ አግኝተው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሰሩ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። በተጨማሪም በአዕምሮ ህመም ሳቢያ ለተለያዩ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት የሚጋለጡ ዜጎች ተገቢውን የጤና እንክብካቤ እንዲሁም የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ በትጋት እንደሚሰሩ መግለጫው አትቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም