የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ በትኩርት እየተሰራ ነው - የግብርና ሚኒስቴር

89
አዳማ ጥቅምት 7/2011 ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ በትኩርት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። የዓለም የምግብ ቀን ''በ2030 ዓ.ም ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የዛሬ ጥረታችን ለነገ ስኬታችን እንረባረብ'' በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይትና በመስክ ምልከታ በሞጆ ከተማ ትናንት ተከብሯል። ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ እንደገለጹት በሀገሪቱ  ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ርብርብ እየተደረገ ነው። ባለፉት ዓመታት በግብርና ሴክተር የኤክስቴሽን አገልግሎትና ግብዓት አጠቃቀም፣ የአዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጅ ማላመድ፣ ማስፋፋትና አተገባበር ዙሪያ የተገኙትን ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አሁን የደረስንበትን በሄክታር 21 ኩንታል የዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነት በሁለተኛው የልማት እቅዱ መጨረሻ ወደ 29 ኩንታል ለማሳደግ ግብ በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። እቅዱን ለማሳካት የግብርና ኤክስቴሽን ፓኬጅን በመከለስና በመፈተሽ አዳዲስ በምርምር የተገኙ አሰራሮች፣ ቴክኖሎጅዎችና ውጤቶችን በየደረጃው በሚገኙ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ዘንድ ተደራሽ የማድረግ ሥራ በሙሉ አቅም እየተሰራ ነው፡፡ በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መጣሉን የጠቀሱት ዶክተር ካባ ለዚህም የተሟላ የኤክስቴሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ቴክኖሎጅ አጠቃቀም መታየቱን ተናግረዋል። ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል በ2012 ዓ.ም መጨረሻ አጠቃላይ ዓመታዊ የዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነትን ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ድህነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ''የዓለም የምግብ ቀን ስናከብር እለቱን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የተቀረፁ መልእክቶችን ለማሳካት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለተሻለ ውጤት የምንተጋበት ነው'' ብለዋል። በዘርፉ የተቀመሩ ተሞክሮዎችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮቹ ዘንድ በአግባቡ ተደራሽ በማድረግና ለተግባራዊነታቸው ሙሉ ድጋፍ በመስጠት በሴከተሩ የተቀመጠውን ግብ ለማሳከት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ናቸው። በአነስተኛ አርሶና አርብቶ  አደሮች ደረጃ ውሃን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማት በማስፋፋት ገበያ ተኮር ሰብል በስፋት ለማምራት ስትራቴጅ ነድፈን እየሰራን ነው ብለዋል። በዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ በበኩላቸው ''ሀገሪቱ በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ የተሟላ የኤክስቴሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ቴክኖሎጅ አጠቃቀም በማጎልበት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት የታየበት ነው'' ብለዋል፡፡ የግብርና ምርቱ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ዘርፉ ለወጣቱ ትውልድ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠርበት፣ በቂ የኢንዱስትሪ ግብዓትና ገበያ ተኮር  ሰብሎች በስፋት የሚመረቱበት እንዲሆን አሁንም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገዝበዋል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም