አፍሪካ የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የተቀናጀ ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈልጋታል

64
  አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 በአፍሪካ የሚፈፀሙ የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የተቀናጀ ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈልጋል ተባለ። የሳይበር ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ዓለም አቀፍ ትብብርና የአቅም ግንባታ ላይ ያተኮረና ለሦስት ቀናት የሚቆይ የአፍሪካ ሳይበር ወንጀል ፎረም  ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አማኒ አቡዘይድ እንደተናገሩት የሳይበር ወንጀሎች በፍጥነትና በብዛት እያደጉ መጥተዋል። ይህም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ፈተና እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት። ወንጀሉን ለመከላከል የአፍሪካ መንግስታት የሳይበር ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የጋራ የተቀናጀ ስትራቴጂና ፖሊሲ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር አማኒ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ስፔስ መፍጠር ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ አምባሳደር ራኒየር ሳባቱሲ በበኩላቸው እንዳሉት የሳይበር ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተባባሱ ነው። 'ይህም በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ እያደገ መጥቷል' ያሉት አምባሳደር ራኒየር ቅድሚያ ሰጥቶ ለመታገል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚውን ዋስትናው የተጠበቀ ለማድረግ የጋራ ፖሊሲና ስትራቴጂ አውጥቶ በቅንጅት መስራት ይጠይቃልም ነው ያሉት። በአፍሪካ ደረጃ ያሉትን የሳይበር ወንጀሎችና ተያያዥ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ወጥ የሳይበር ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የጋምቢያ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ሚኒስትር ኢብሪማ ሲላህ ናቸው። 'ጋምቢያ የዘርፉን ወንጀሎች ለመከላከል እየሰራች ነው' ያሉት ሚኒስትር ኢብሪማ በአፍሪካ ደረጃ በትብብር ካልተሰራ 'የሳይበር ወንጀል ለአህጉሩ ኢኮኖሚ አደጋ አለው' ብለዋል። የናይጄሪያ ብሔራዊ ሸንጎ ሴናተር ፎስተር ኦጎላ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ የፍትህ ዘርፍ አካላት ስለ ሳይበር ወንጀሎች ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በናይጄሪያ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ህግ እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች በሳይበር ወንጀሎች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በመላው አፍሪካ ይህን ዓይነት አስተሳሰብን የመቀየር ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል። የአፍሪካ የፍትህ አካላት በሳይበር ወንጀሎችና በኤሌክትሮኒክስ መረጃ ዙሪያ ያላቸውን አቅምና ግንዛቤ ማሳደግ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ስለመሆኑ በኮንፈረንሱ ተገልጿል። የሳይበር ወንጀሎችን ለመቀነስ አፍሪካ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገሮች ጋር ተባብራ ልትሰራ እንደሚገባትም ተነግሯል። ታማኝ የሳይበር ልማት ለመገንባት ያለመውን የአፍሪካውን የማላቦ የሳይበር ኮንቬንሽን ስምምነት መተግበርን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት በዘርፉ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም