የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ከነገ በስቲያ ይጀመራል

85
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ከነገ በስቲያ ይጀመራል። ለ13ኛ ጊዜ በሚካሄደው አውደ ርዕዩ "ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን" በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል። የዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት አውደ ርዕዩ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የስራ ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው። አውደ ርዕዩ ተማሪዎች ወደ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ከመቀላቀላቸው በፊት ስራዎቻቸውን ለህብረተሰቡ፣ ለመንግስት ተቋማትና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን ተናግረዋል። ተማሪዎቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ከመቅረፍ አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት። አውደ ርዕዩ በየዓመቱ ሲካሄድ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ሰው እንደሚጎበኘውና ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በአውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ የትምህርት ክፍሉ 60 ተማሪዎች የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የተሻለ ስራ ያቀረቡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ማህበር በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል። በዚህ አውደ ርዕይ ሌሎች የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል። አውደ ርዕዩ ከጥቅምት 8-11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም