ስሎቫኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የቢዝነስ ትስስር ለመፍጠር ትሰራለች- ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር

53
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 ስሎቫኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የቢዝነስ ትስስር ለመፍጠር ትሰራለች ሲሉ የስሎቫኒያው ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር ተናገሩ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው የስሎቫኒያ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የስሎቫኒያ ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆርን በብሄራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ላይ በጋራ መክረዋል። ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ገለጻ፤ በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ጉብኝት "በስሎቫኒያና አፍሪካ ግንኙነት አዲስ ታሪክ የከፈተ ነው"። ኢትዮጵያ የጎበኙ የመጀመሪያው የስሎቫኒያ ፕሬዝዳንት በመሆናቸው መደሰታቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ጉብኝታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ስሎቫኒያ በበርካታ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተመሳሳይ አቋም ማራመዳቸው ለጉብኝታቸው መነሻ መሆኑንም አክለዋል። ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለእርቅ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንግድ በመፍታት ረገድ ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት አንዳላቸው መገንዘባቸውንም አክለዋል። ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በነበራቸው ውይይትም ሁለቱ አገራት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በጋራ ለመስራት እንደተስማሙ ገልጸዋል። በስሎቫኒያና በኢትዮጵያ መካከል የንግድ ትስስርን የሚያጠናክር የቢዝነስ ፎረም እንደሚደረግ ተናግረው፤ "ይህ አውን አንዲሆን ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኢትዮጵያ ቢዝነስ ልዑክ ይዘው  ስሎቫኒያን አንዲገበኙ ጋብዣቸዋለሁ" ብለዋል። ስሎቫኒያ አፍሪካ ጋር ለምታደርገው ግንኙነት ኢትዮጵያ መግቢያ በር  እንደሆነች ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከስሎቫኒያ በተጨማሪ ከባልካን አገራት ጋር ጠንካራ ትስስር እንድትፈጥር የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ እድገት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስታውሰው፤ የስሎቫኒያ ባለሃብቶች ይህን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያም በሁለቱ አገራት ያለው ትስስር ይበልጥ አንዲጎለብት ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደምትሰራም አውስተዋል። "መስከረም ከገባ በኋላ ባሉት ቀናቶች ሁለት የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ሃላፊዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው አገሪቱ ያላትን ተቀባይነት ያሳያል" ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ናቸው። ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር በቅርቡ ስሎቫኒያ በአዲስ አበባ ኢምባሲዋን ለመክፈት እያጤነች መሆኑን መግለጻቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ስሎቫኒያ የቀድሞ ዩጎዝላቪያ አካል የነበረች ስትሆን፤ የፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር የኢትዮጵያ ጉብኝት ስሎቫኒያ እንደ አገር ከተመሰረተች በኋላ በአገር መሪ ደረጃ ከሰሃራ በታች የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው ተብሎለታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም