ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ከጉዳት የሚታደጉ የቅርስ ሃኪሞች ማፍራት ያስፈልጋል ፡- የመስኩ ተመራማሪዎች

55
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 ኢትዮጵያ የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ቅርሶቿን ጠብቃ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የቅርስ ተመራመሪዎችና ቅርሶችን ከውድመት የሚታደጉ የቅርስ ሃኪሞች ማፍራት እንደሚጠበቅባት የመስኩ ተመራማሪዎች አመለከቱ። ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ባላት የረጅም ዘመን ታሪክ ለቁጥር የሚያዳግቱ አያሌ ተዳሳሽና የማይዳሱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለጸጋ ናት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪኦሎጂና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሌ ሃጎስ ከዛሬ ሰባት ሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ ላሉት የማንነት መገለጫ የሆኑ የቅርስ ሀብቶች ተገቢው እውቅና፣ እንክብካቤና ጥበቃ እንዳልተደረገ ይናገራሉ። ሌላው ባልደረባቸው ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ብትይዝም በቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ተግባር ግን አስፈላጊውን ስራ እየሰራች አለመሆኑን ያነሳሉ። ''ቅርሶች የማንነት መገለጫ፣ የታሪክ ሽማግሌዎች ናቸው'' የሚሉት ምሁራኑ በኢትዮጵያ ካለው የቅርስ ብዛት አኳያ ተገቢው ጥናትና ምርምር፣ ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ በቂና ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት አለመቻሉን ጠቁመዋል። በዚህም ዓለምን ያስደነቁ የታሪክ አሻራ ቅርሶች ተገቢው እንክብካቤ፣ ጥበቃና እድሳት ስላልተደረገላቸው በእድሜ ብዛት ለአደጋ እየተጋለጠ መሆኑን፣ በመፍትሄነት የተወሰዱ የጥበቃ እርምጃዎችም ቅርሶችን ለተጨማሪ ጉዳት እየዳረጉ መሆኑን አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ቅርሶች የከፋ አደጋ ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት ምሁራኑ፤ በተለይም በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶችን ለመጠገን የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች በቅርሶች ላይ ሌላ ስጋት እየደቀኑ እንደሆነ ነው ያብራሩት። ቅርሶችን በተገቢው መልኩ ለመንከባከብና ለመጠበቅ ብሎም ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የአገር ውስጥ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ስለሆነም ቅርሶችን ለልማት ለማዋል፣ መመዝገብ፣ ጥናት ምርምር ማድረግ፣ የማህበረሰቡን ግንዘቤ ማሳደግ፣ በትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችን ማፍራትና መካነ ቅርሶችን የጥናትና ምርመር ማዕከል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ይህም አገሪቱ ካላት ቅርሶች ብዛት አንጻር ተገቢወን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለስራ እድል ፈጠራም የጎላ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል። ዘርፉን የሚመሩ ሃላፊዎችም ሙያዊ እውቀት ያላቸው እንጂ በዘፈቀደ የሚሾሙ ግለሰቦች መሆን እንደሌለባቸውም ገልጸዋል። የብሔራዊ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ በበኩላቸው የአርኪኦሎጂ ጥናትና ምርምሮች ከባድና ከፍተኛ ፉክክሮች የሚጠይቁ በመሆናቸው የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች በአገር ውስጥ ተቋማት የተወሰኑ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። በመካነ ቅርሶች ላይ የሚደረጉ የአርኪኦሎጂና ፓሊኦንቶሎጂ ጥናትና ምርምሮች የተወሰኑ የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ከውጭ የምርምር ተቋማት ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት ሲሰሩ እንደቆዩ አስታውሰዋል። ወደፊት በአገር በቀል ቅርሶች ላይ ተግባራዊ ስልጠናዎች እንዲሰጡ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ክፍሎች መከፈት መጀመራቸውን በማንሳት፣ ባለስልጣኑ እንደቅርሱ አይነት ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከወጭ የሚመጡ ሙያተኞችን በመተካት በእድሜ ምክንያት ዘርፈ ብዙ አደጋ ለተጋረጠባቸው የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም