ብሄራዊ አርማው ለምን የግጭት መነሻ ሆነ?

73
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብሄራዊ አርማ ዙሪያ ዜጎች የጋራ መግባባት ላይ ካልደረሱ ጉዳዩ የግጭት መንስኤ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው ሲሉ አስተያየተ ሰጪዎች ተናገሩ። ዛሬ የተከበረው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ክብረ በዓል እንደከዚህ ቀደሙ በአደባባይ አልተከበረም። ክብረ በዓሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት ተቀሟት ነው የተከበረው። በዓሉ በአደባባይ ያልተከበረው በአገሪቱ ከሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እየተስተዋለ ያለውን አለመግባባትና ግጭት ለማስወገድ ሲባል መሆኑን የበዓሉ አዘጋጆች ገልፀዋል። ያለመግባባት መንስኤ እየሆነ ያለው አርማ፤ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ እና ከታች ቀይ ቀለም ባለው የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ መሃል ላይ የሰፈረውና በቀጥታና እኩል መስመሮች የተዋቀረ ኮከብና በመስመሮቹ መተላለፊያ ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ጨረር የሚያይበት ምስል ነው። "ይህ አርማ ለምን የግጭት መነሻ ሊሆን ቻለ? " ብሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው ግለሰቦች የተለያዩ ምላሾችን ሰጥተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ባለውን ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ አርማ ላይ ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ተናግረዋል። የህግ ባለሙያው አቶ ዘፋኒያ ዓለሙ አሁን ባለው የአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ "ሰንደቅ ዓላማ ላይ የግዴታ ብሄራዊ አርማ ሊኖረው ይገባል የሚለው የህገ-መንግስቱ ድንጋጌ ችግር እየፈጠረ ነው" በማለት ይገልጻሉ። ከዚህም ባለፈ አርማው በአዋጅ ተደንግጎ ተግባራዊ ሲደረግ በቂ የህዝብ ውይይት አልተካሄደም፤ ስራ ላይ ከዋለ በኋላም ቢሆን ዜጎች የአርማውን ትርጉም በአግባቡ እንዲረዱት አለመደረጉን እንደ አንድ ምክንያት አንስተዋል። በመሆኑም ጉዳዩ ለህዝብ ቀርቦ ሊመከርበትና መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ነው የህግ ባለሙያው ያሳሰቡት። የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዝዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራውም በአርማው ዙሪያ ያለው የዜጎች ግንዛቤ በእጅጉ አነስተኛ መሆኑን ይቀበላሉ። እንደሳቸው እምነት ዜጎች ስለአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ አርማ በቂ ግንዛቤ አለመያዛቸው ነው ጉዳዮን የግጭት ምንጭ እያደረገው ያለው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አባድር ፋሪስ እና አቶ ተክሌ ተሰማ በበኩላቸው አሁን አገሪቷ እያሳየችው ካለው ለውጥ ጋር ተያይዞ በሰንደቅ ዓላማው አርማ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው አዲስ ነገር አለመሆኑን ነው የገለጹት። መንግስት በየደረጃው ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በማወያየት ህብረተሰቡ የተስማማበትንና የጋራ መግባባት ላይ የደረሰበትን አርማ አድርጎ ማጽደቅ የሚቻል መሆኑንም ተናግረዋል። 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፓናል ውይይት ተከብሯል። ምክር ቤቱ  11ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በብሄራዊ መግባባትና ስምምነት ላይ በሚያደርሱ ውይይቶች እንደሚከበር ማስታወቁ ይታወሳል። በዓሉ በሰንደቅ አላማው ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የሚከናወንበትና የተለየ አመለካከትን ለማስተናገድ እድል በሚፈጥር መልኩ እንደሚከበርም ተገልጿል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም