የፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ወጥ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ተባለ

102
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ወጥ የሆነ የጋራ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገለጸ። 47 አገሮችን ያቀፈው በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድን ለሁለት ቀን የሚቆየውን ስብስባ ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል። የተደራዳሪ ቡድኑ ስብስባ አላማ ከህዳር 24 እስከ ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በፖላንድ ካቶዊስ ከተማ በሚካሄደው 24ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን አገሮቹ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው 21ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የዓለም አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መከላከል የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ያም ቢሆን ስምምነቱ በፍጥነት ተግባራዊ አለመሆኑ እንደሚያሳስባቸው የአየር ንብረት ለውጡ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያደርስባቸው የሚገልጹት በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያነሱት ሀሳብ ነው። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ የድርድሩ ጊዜ አብቅቶ የፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል። በስምምነቱ መሰረት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አገሮች ሰፋፊ የጉዳት ማገገሚያ ቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ተጎጂ አገሮች ጉዳታቸውን የሚቋቋሙበት ድጋፍ እንዲደረግላቸው የተነሱ ሀሳቦች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። ለዚህም 47ቱ አገራት አንድ የሆነ የጋራ ድምጽ ሊኖራቸው እንደሚገባና ጉባኤውም ይህን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድንን በሊቀመንበርነት እየመራች መሆኗንና አገሮቹ አንድ አቋም እንዲኖራቸው ሀሳብ የማደራጀት ስራ እያከናወነች እንደሆነ ዶክተር ገመዶ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ሊቀመንበርነቷ በፈረንጆቹ 2018 እንደሚጠናቀቅና ባለው ቀሪ ጊዜ አገሮቹ ወጥ አቋም ይዘው እንዲወጡ ጥረት እንደምታደርግና በፖላንዱ ጉባኤ ላይ የ47ቱን አገሮች የጋራ አቋም እንደምታስተላልፍም አክለዋል። የኡጋንዳ የውሃና የአካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኪቱቱ ኪሞኖ በበኩላቸው በፖላንድ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የታዳጊ አገሮቹ መልዕክት በሚገባ እንዲተላለፍ በጉባኤው የጋራ አቋም ይዘውና ተስማምተው መውጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በኢኮኖሚ ያላደጉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጡ ተጎጂዎች መሆናቸውን አመልክተው ከቀናት በፊት በምስራቅ ዩጋንዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን 43 ሰዎች መሞታቸውንና ይህ አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል። ለፖላንዱ ጉባኤ አገራቱ ጠንካራ የሆነ አንድ አቋም ከያዙ ተጽእኖ ማሳደር እንደሚችሉም ገልጸዋል። የቡታን ብሔራዊ የአካባቢ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሶናም ዋንግዲ አገራቸው በ2019 ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድን ሊቀመንበርነትን እንደምትቀበል ጠቅሰዋል። በሊቀመንበርነቷ ወቅት የቡድኑ አባል አገሮች ከፓሪሱ ስምምነት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የምትሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በኢኮኖሚ ያላደጉ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ በመሆኑ የበለጸጉ አገሮች ለጉዳዩ ተጫባጭ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ጠይቀዋል። የ20 አገሮች የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሮች እንዲሁም የተቀሩት አገሮች ተወካዮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በስብሰባው ማጠናቀቂያ አገሮቹ የጋራ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጡ በስብሰባው መክፈቻ ወቅት ተገልጿል። የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድኑ ከፓሪሱ የአየር የንብረት ለውጥ ስምምነት በኋላ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ጥቅም ለማስከበር የተቋቋመ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም