በኢሉአባቦር ዞን በገጠር በስራ እድል ፈጠራ ለተሰማሩ ወጣቶች የእርሻ መሬት ተከፋፈለ

82
መቱ/ነቀምቴ -ረጋሳ  ግንቦት 13/2010 በኢሉአባቦር ዞን በገጠር የስራ ዕድል ፈጠራ ለተሰማሩ ወጣቶች ከ2 ሺ200 ሄክታር በላይ መሬት መከፋፈሉን የዞኑ ስራ ዕድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በቄለም ወለጋ ዞን ደግሞ ባለፉት ስምንት ወራት ከ26 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና ከተማ  የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌታቸው አብዲሳ እንዳሉት የእርሻ መሬቱ የተሰጠው በዞኑ በ1ሺ119 ማህበራት ተደራጅተው በግብርና  ለተሰማሩ 9ሺ 800 በላይ ወጣቶች ነው፡፡ በቡሬ፣ ዳሪሙ፣ ቢሎኖጳና ዶረኒ ወረዳዎች ለሚገኙት ለእነዚሁ ወጣቶቹ የተሰጠው የእርሻ መሬት በአብዛኛው  ለሰሊጥ፣ ሩዝ ፣ አደንጓሬ፣ በቆሎና የመሳሰሉ ገበያ ተኮር ሰብሎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለወጣቶቹ ከተሰጠው መሬት ውስጥ ከ1ሺ 200 ሄክታር በላይ የሚሆነው ከዚህ ቀደም ለግብርና ልማት ያልዋለ ባዶ መሬት መሆኑን ገልጸው ቀሪው በገቡት ውል መሠረት ወደ ልማት ካልገቡ ባለሀብቶች ተነጥቆ ለወጣቶች የተላለፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእርሻ ልማትን ጨምሮ በእንስሳት ማድለብና ሌሎች የግብርና መስኮች ለተሰማሩ ለእነዚሁ ወጣቶች ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ ተሰጥቷል፡፡ የማህበሩ አባላት ለልማቱ የሚሆን በቂ መሬት በማግኘታቸው ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ህይወታቸውን ለመቀየር እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወጣት ኦብሳ አራርሶ  በቡሬ ወረዳ ቶሊ ጬካ ቀበሌ  በማህበር ተደራጅተው በግብርናው የስራ እድል ፈጠራ ከተሰማሩ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚለው ከሌሎች አስር ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ባገኙት ከአራት ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ እና ሩዝ ለማልማት ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ “በዘመናዊ መልኩ እንድናለማ ትራክተር ተገዝቶ ተሰጥቶናል” ያለው ወጣቱ ገበያ ተኮር ሰብሎችን በማልማት ራሳቸውን ለመለወጥ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡ “ከዚህ ቀደም የእርሻ ማሳ ስለሌለኝ ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር የእኩል እሰራ ነበር” ያለው ደግሞ ሌላኛው  ወጣት ረታ ሙለታ  ነው፡፡ በዞኑ 13 ወረዳዎች የግብርናውን መስክ  ጨምሮ በግንባታ፣ ከተማ ግብርና፣ አገልግሎትና የመሳሰሉት መስኮች ከ21 ሺ 300 በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ እስከ አመቱ መጨረሻም ከ28ሺ በላይ ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች በማህበር በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ከዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቄለም ወለጋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ከ26ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ለሊሣ ቀኖ እንዳስታወቁት በዞኑ 11 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት በ2 ሺህ 390 ኢንተርፕራይዞች  በመደራጀት ነው፡፡ ለወጣቶች ከመደበኛና ከተዘዋዋሪ ብድር 90 ሚሊዮን ብርና 990 ሄክታር የመስሪያ እና የመሸጫ መሬት መመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል በ2ሺህ 410 ኢንተርፕራይዞች  ለተደራጁ 12ሺህ 500 አባላት የ180 ሚሊዮን ብር  የገበያ ትስስር  የተፈጠረላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የደምቢ ዶሎ ከተማ 06 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ታሪኩ ሰንበቶ በሰጠው አስተያየት ከሦስት ወር በፊት አምስት ሆነው በመደራጀት ባገኙት የ150 ሺህ ብር ብድር የምግብና የመጠጥ ግሮሰሪ ከፍተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ''ማንም ሰው ጠንክሮ ከሰራ ከድህነት በመውጣት ባለሀብት መሆን ይቻላል'' ያለው ወጣት ታሪኩ የጀመሩትን ሥራ ተግተው በመሥራት ሀብት ለማፍራት ዓላማ አድርገው መነሣታቸውን አስረድቷል፡፡ ለስድስት  ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠር  መቻላቸውንም  ተናግሯል፡፡ በዳሌ ሰዲ ወረዳ የሐሮ ሰቡ ከተማ ''መገርሣና ጂጄ '' በሚል መጠሪያ የተደራጁ ወጣቶችም ወደ ሥራ ገብተው ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የኢንተርፕራይዙ ሊቀመንበር ወጣት መገርሣ ኬኔሣ እንደተናገረው ከመንግሥት በተመቻቸላቸው የ134 ሺህ ብርና ራሳቸው በቆጠቡት 13 ሺህ ብር ባጃጅ ገዝተው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ ሥራውንም በጥሩ ሁኔታ እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም