የአየር ጸባይ መረጃን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ለመተግበር የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

82
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 የብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለህብረተሰቡ የዝናብና የአየር ጸባይ መረጃ በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርግበት "ማፕሩም" የተባለ ዲጂታል አሰራር ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀመረ። ኤጀንሲው ከአለም አቀፍ የአየር ንብረት ምርምርና ማህበረሰብ ተቋም ጋር በመተባበር ለጤና፣ ለግብርናና ለአደጋ መከላከል ባለሙያዎች ነው ሥልጠናውን እየሰጠ ያለው። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ጊዜ ለኢዜአ እንደለገለጹት፤ ስልጠናው የትንበያ፣ የጤና፣ የአደጋ መከላከልና የግብርና አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው። ይህም ኤጀንሲው በየሳምንቱ፣ በየ10 ቀኑ፣ በየወሩ፣ በየዓመቱና ወቅትን መሰረት አድርጎ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ያለምንም ገደብ ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ጠቁመዋል። አገልግሎቶቹ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከሳተላይት ጋር በማቀናጀት የሚሰጥ ሲሆን ተጠቃሚዎች በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው  በአራት ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚፈልጉትን የቦታና የአካባቢ አገልግሎት በቅርበት ማግኘት ያስችላቸዋል ሲሉም አክለዋል። በኢትዮጵያ እኤአ በ2014 አገልግሎቱን መስጠት እንደተጀመረ አስታውሰው ስልጠናው በአገልግሎቱ ወቅት የታየውን ክፍተት ለሙላትና የበለጠ ለማሳደግ እንደሚያስችል አቶ ፈጠነ ተናግረዋል። ከአለም አቀፍ የአየር ንብረት ምርምርና ማህበረሰብ ተቋም የመጡት ዶክተር ቱፋ ድንቁ በበኩላቸው ስልጠናው መረጃን በጥራት ለመሰብሰብ፣ ለመተንተንና ለማሰራጨት የሚያስችል ስራ ለመስራት እንዲያግዝ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይም ከዝናብና ከአየር ጸባይ ጋር ለሚመጡ የጤና፣ የውሃ፣ የግብርና፣ የአቪየሽን፣ የአደጋ መከላከልና የመሰላሉትን አገልግሎቶች መረጃዎቹን በስፋት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ነው። ሰልጣኞቹ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል ለሚገኙ የልማት ሰራተኞች እንዲያሰለጥኑና በመረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔና ተግባር እንዲፈጽሙ ለማሳቻልም እንደሆነ አክለዋል። በኢትዮጵያ የሚትዎሮሎጂ አገልግሎት በ1973 ዓ.ም እንደተጀመረ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም