በሰላም ፎረም ኮንፈረንስ ከነባር ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ አግኝተናል... የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ተሳታፊዎች

69
ሚዛን ግንቦት 13/2010 በደቡብ ክልል ለሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተዘጋጀው የሰላም ፎረም ኮንፈረንስ ልምድ መቅሰማቸውን በክልሉ ከሚገኙ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ገለጹ። የትምህርት ተቋማቱ የተሳተፉበት የሰላም ፎረም ኮንፈረንስ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በቅርቡ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉ የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ፎረም አባላት ተማሪዎችም ለኢዜአ እንዳሉት በመድረኩ ከነባሮቹ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድና ተሞክሮ ቀሰመዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተሳታፊዎች መካከል የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሠላም ፎረም አባል ተማሪ ረሽድ አህመድ እንደለጸው ዩኒቨርሲቲው ገና ጀማሪ በመሆኑ የሠላም ፎረም አደረጃጀት የተጠናከረ አይደለም፡፡ "በመድረኩ በተማሪዎች መካከል ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት እንዴት መከላከል እንደሚቻልና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እንዳይባባሱ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ግንዛቤ ያገኘሁበት ነው" ብሏል፡፡ የሠላም ፎረሙ ለመማር ማስተማር ሥራው ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን በመድረኩ ግንዛቤ በመያዙ በቀጣይ ወደመጣበት ዩኒቨርሲቲ ሲመለስ የሰላም ፎረምን ለማጠናከር ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ "በመድረኩ በተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከነባር ዩኒቨርሲቲ ልምድ እግኝቼበታለሁ" ያለችው ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነጻነት ዘሪሁን ናት፡፡ እንደ ተማሪዋ ገለጻ ፣ በተማሪዎች የሚቋቋሙ የሠላም ፎረሞች ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቀድሞ ተረድቶ ዝግጅት ለማድረግና ሲከሰቱም በአግባቡ ለመከላከል አጋዥ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ግጭቶች የሚከሰቱት በተማሪዎችና በዩኒቨርሲቲ አመራሩ መካከል መራራቅ ሲኖርና የመረጃ ክፍተት ሲፈጠር መሆኑንም አስረድታለች፡፡ "ክፍተቱን ለማጥበብና ችግሮች ሲፈጠሩ ፈጥኖ መፍትሄ ለማበጀት የሠላም ፎረሞች ከፍተኛ ሚና አላቸው" ስትል ገልጻለች፡፡ "በቀጣይ በዩኒቨርሲቲያችን ጠንካራ የሠላም ፎረም እንዲመሰረት እንሰራለን" ያለው ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እስራኤል ታምራት ነው፡፡ መድረኩ ነባሮቹ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶችን እንዴት መከላከልና መቆጣጠር እንደቻሉ የተረዳበት ኮንፈረንስ መሆኑን ገልጾ፣ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሠላም ማዕከላት ለመሆን መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ ለሠላማዊ መማር ማስተማር ጉልህ ድርሻ ያላቸው የሠላም ፎረሞችን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማደራጀት ተገቢ መሆኑንም ነው ተማሪ እስራኤል የገለጸው፡፡ የግጭት ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ ለይቶ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሞ፣ ለእዚህም እርሱን ጨምሮ  የሠላም ፎረም አባላት እንደተማሪም እንደአመራርም ሆነው መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም