በመንግስት ጥሪ አገር ቤት ከገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበው አንድ ፓርቲ ብቻ ነው

128
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ከገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በአገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እውቅና እንዲሰጠው የጠየቀው አንድ ፓርቲ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በውጭ አገራት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማካሄድ እንዲችሉ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ፓርቲዎች ወደአገር ቤት ተመልሰዋል። እነዚህ የፖለቲካ ማህበራት በአገሪቱ የምርጫ ህግ መሰረት ተመዝግበው ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ከምርጫ ቦርድ ጋር በምርጫ ህግ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅና ለመመዝገብ በሚያስፈልጉ መስፈርቶች ዙሪያ ቀደም በሎ ውይይት አካሂደዋል። ይሁን እንጂ ወደ አገር ከገቡት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበው "የአፋር  ህዝብ ፓርቲ” በሚል ስያሜ የሚጠራው የፖለቲካ ድርጅት ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለኢዜአ ገልጿል። የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም አባይ እንደገለጹት ፓርቲዎቹ በህጋዊ መንገድ እንዲመዘገቡ እየተጠበቀ ቢሆንም ከተጠቀሰው ውጭ ሌሎቹ እስካሁን ጥያቄ አላቀረቡም። ፓርቲዎቹ በቦርዱ ተመዝግበው ህጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ቦርዱ ጥሪ ማድረጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ የአገሪቱ ህጎች፣ የቦርዱ አዋጆችና መመሪያዎች ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ፓርቲዎች በህጉ መሰረት ምዝገባ ለማካሄድ ቦርዱ ዝግጁ ነው ብለዋል። የምዝገባ ጥያቄ ለሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ህጋዊ እውቅና የሚሰጠው የሚያቀርቡት ደንብና ፕሮግራም ከአገሪቱ የምርጫ ህጎች አንፃር ታይቶ መሆኑን አቶ ተስፋዓለም አስረድተዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ለመመዝገብ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ ቢያንስ ከአራት ክልሎች የተሰበሰበ 1 ሺህ 500 የድጋፍ ፊርማ፤ በክልል ደረጃ ለሚመዘገብ ደግሞ 750 የድጋፍ ፊርማ አሰባሰቦ ማቅረብ እንዳለበት በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/ 2000 ተደንግጓል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት 22 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 40 ክልላዊ ፓርቲዎች የቦርዱን ህጋዊ እውቅና አግኝተው በአገር ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እያካሄዱ ይገኛሉ። የመንግስትን ጥሪ ተከትለው ወደ አገር ከገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦዴግ፣ ዴምህት፣ የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር እና ኦብነግ ይገኙበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም