የጉለሌ ክፍለ ከተማ ባለፉት 5 ዓመታት በ317 ሚሊዮን ብር ወጪ ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ

86
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከ2006 እስከ 20010  ድረስ ባሉት 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በ317 ሚሊዮን ብር ወጪ ያከናወናቸውን 202 ፕሮጀክቶች አስመረቀ። በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ተጠቁሟል። የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሀ ክፍለ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የክፍለ ከተማው ባለ 4 ፎቅ የአስተዳደር ህንጻ፣ 85 ሼዶች፣ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች፣ መጸዳጃ ቤቶችና ሌሎች ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። በተያዘው በጀት ዓመት 73 ነባር ፕሮጀክቶችና 41 አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን እቅድ መያዙን አቶ ፍሰሀ ጠቁመዋል። የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስና በአገሪቱ ከተጀመረውን የለውጥ ሂደት ጋር አብሮ የሚሄድ መዋቅር ለመፍጠር በክፍለ ከተማው አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በክፍለ ከተማው በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የውሀና የመብራት መጥፋት ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የቱሪዝም አገልግሎትን በማሳደግ የከተማው ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም