ለድርጅታዊ ጉባኤው ውሳኔዎች ስኬት የባለድርሻዎች ሚና

1818

ደሞዝ አያሌው/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ ግምት የተሰጠው፣ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችም በጉጉት የሚጠበቁ  ነበሩ።

የተጀመረው ለውጥና የተገኘው ውጤትም የሚደነቅ በአገር ቤት ብቻም ሳይሆን በዲፕሎማሲው ዙሪያም በብዙዎች ዘንድ ትልቅ የተስፋ ብርሀን ጭላንጭልን ያሳየ ነው።

በሀገሪቱ ባለፉት 5 ወራት የተከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ የሰላምና የስራ እድል ፈጠራ ችግሮችን የሚፈቱ አቅጣጫዎችን ጨምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ኢትዮጵያዊ አንድንትን የሚያጎለብቱ ምክክሮች በመደረጋቸው ለተግባራዊነቱ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃላፊዎችና የህብረተሰብ አደራጃጀት አመራሮች አብራርተዋል፡፡

የተጀመረው ለውጥና የእድገት አቅጣጫ የምሁራንን ዕውቀት፣ ልምድና ችሎታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፈልገው እንደሆነና ለውጡ የታለመለትን ውጤት እንዲያሳካ በጥናትና ምርምር ስራዎች እና ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠት ምሁራን ለሀገሪቱ የማይተካ ሚና እንዲያበረክቱ ጉባኤው ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

የኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የህዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች የነበሩ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የፍትህ፣ የስራ እድል፣ የሰላም መስፈን ፣የህግ የበላይነት መከበር ላይ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ በስፋት ተወያይቶ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው የገለጹት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሚሳ ናቸው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ እየታየ ያለው ለውጥ ገና ሂዴት ላይ ያለ በመሆኑ የተቀናጀና የተጠናከረ ስራ ከህብረተሰቡም ሆነ ከአመራሩ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ፍቅሬ አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔዎቹ የዜጎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሀገራዊ እድገትን ለማስመዝገብ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን የያዙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ የመደመር መርህን ይዞ  አንድነቱንና ልማትን በማጠናከር ከመሪው ብቻ መጠበቅ ሳይሆን ሁሉም የራሱን ሚና መጫወት ይኖርበታል ሲሉም ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጡ አካል በመሆናቸው ፣ የድርሻችንን መወጣት የምንችልው እንዴት ነው ? በሚሉ ነጥቦች ላይ በጥልቀት በመምከር ለሪፎርሙ ስኬታማነት የጎላ ድርሻ ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማሩ ሂደት የታቀዱ ተግባራትን ከማሳካት ጎን ለጎን በሀገሪቱ በማንኛውም አካል መካከል ልዩነቶች በሚስተዋሉበት ወቅት ተመካክሮ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻሉባቸውን አቅጣጫዎችና በጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለፖሊሲ አውጪዎች ጭምር ማመላከት እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር ፍቅሬ የጠቆሙት ፡፡

ባለፉት 5 ወራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው የሚቀርቡለትን አቅጣጫዎች ማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ጠብቄ ነብር ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቪርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኑርልኝ ተፈራ ናቸው፡፡

ምሁራን በለውጡ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱና ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እንዲያካሂዱ ቀጣይነት ያለው የተረጋጋ ሰላም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዩንቨርሲቲዎች ሰፋፊ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ስራዎች መካሄድ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ ናቸው፡፡

የኢህአዴግ ጉባኤ ለምሁራን ተሳትፎ የሰጠውን ትኩረት የሚመጥንና ለሀገራዊ እድገት ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናውን  ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ የተቀመጠውን የምሁራን ድርሻ በመወጣት የትምህርት ተቋማት በእውቀትና በስነምግባር የታነጹ ባለሞያዎችን ማፍራት ላይ በስፋት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ግብርናን የሚያዘምኑና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የመርምር ውጤቶችን በማውጣት ሀገሪቱ በስፋት እየገባችበት ላለው የኢንዱስትሪ ልማት በቂ ግብአት የሚቀርብበትን ሂደት ለሚያሳኩ ተግባራት እገዛ ለማድርግ  መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አዱሱ አመራር ባለፉት 5 ወራት ባከናወናቸው ተግባራት ሀገራዊ መረጋጋት በማምጣት በአንድንት ላይ የሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑንና በመደመር ሀገርን ማሳደግ እንደሚቻል መግባባት ላይ የተደረሰ በመሆኑ በቀጣይም ከህዝቡ ጋር በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

ኢህአዴግ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ማጠናቀቂያ አንዱ ጥሪ ያደረገው ለምሁራን በመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ምሁራን የበኩላቸውን ለማበርከት እንደሚፈልጉ ባለፉት 5 ወራት የታዩ ፍላጎቶች ማሳያ መሆናቸውን የጠቀሱት የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ አንዱ የለውጥ ጉዳይ የሰላምና መግባባት ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ምሁራን ስለ ሰላም ማስተማር፣የወጣቱን የስራ አጥንት መፍቻ ሀሳብና የህግ የበላይንት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናትና ምርምር ድጋፍ ማድረግ ላይ ምሁራን ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን በመረዳ ድርጅቱ በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርቧል ብለዋል፡፡

በሃገር ውስጥም ሆን ከሀገር ውጪ ያሉ ምሁራን በሀገሪቱ ከሚገነባው ዴሞክራሲ ጎን ለጎን ልማትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሀሳቦችን የማፍልቅ ስራን እንዲሰሩ ምቹ መደላድል የመፍጠር ስራ በተያዘው ዓመት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድና ወደ ውጤት የሚቀየሩበትን ሂደቶች በማመቻቸት  ምሁራን ጠንክረው በመስራት ህብረተሰቡ በተግባር እንዲጠቀምባቸው ማድርግ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከጥፋ የታደጉ ወጣት መሪዎች አግኝታለች ያሉት የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው ከዛሬ ስድስት ወር በፊት በሃገሪቱ ውስጥ በነበረው የሰላም ችግር ህዝቡ ስጋት ውስጥ የነበረበትን ወቅት በትውስታ አንስተዋል፡፡

ሀገሪቱ ከዚህ በፊት በነበራት ታሪክ ስልጣን ላይ የነበረ አካል ለሌላ በሚያስረክብበት ወቅት የነበሩ መጠፋፋትን ወደ ፍቅርና ይቅርታ በመቀየር በሰላማዊ መንገድ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በተግባር እያየን ያለንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

ሀገሪቷን ተደቅኖባት ከነበረው አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ የታደጉ ወጣት መሬዎችን አግኝታለች፤ኢትዮጵያ ዛሬም ታሪክ ሰሪ ልጆች እንዳፈራች በተግባር ያየንየበት ወቅት ላይ በመሆናችን ደስ ብሎኛል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤በቀጣይ መንግስት ትኩረት ቢያደርግባቸው ያሏቸውን ሃሳቦችም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡-

አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታየውን የሰላም ችግር ለመቅረፍ በቦታው እየሄዱ ማስተማር እንደሚገባና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ከህግ በታች መሆኑን በተግባር ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለወጣቱ የስራ እድል የማመቻቸት ስራ ላይ መጠንከር ከመንግስት ይጠበቃል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“እኔ ኢትዮጵያዊነት በርካታ ቋንቋንና ባህልን የያዘች ትልቅ ሀገር መሆኗ የተንጸባረቀበትና የተረዳሁባት ጉባኤ ነው ስትል የሀዋሳ ቆይታዋን የምትገልጸው ደግሞ በተጋባዥነት የተሳተፈችው ደራሲና ጋዜጠኛ እምወድሽ በቀለ ናት ፡፡

ከሰላም ብዙ ማትረፍ ይቻላል ያለችው ደራሲ እምወድሽ ፤ “ደራሲያንም ሆነ ምሁራን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ሀገር ወዳድነት እንዲያድግ የሰራነው ስራ አናሳ በመሆኑ በቀጣይ ጠንክረን ለአዲሱ ትውልድ ማሳወቅ ይጠበቅብናል ስትል ነው አስተያየቷን የሰጠችው፤በቀጣይ የሚጠበቅባትን ለመስራት መዘጋጀቷን በመግለጽ፡፡

ለሀግር ፍቅርና ክብር  ሁሉም በሚችለውና ባለው ሞያ መስራት ያስፈልጋል በማትም ደራሲ እምወድሽ ምልእክቷን አስተላፋለች፡፡

ኢህአዴግ “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ ባካሄደበት ወቅት በሀገሪቱ ከተደረገው የአዲስ አስተሳሰብ ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የመሪነት ሚናውን ለመወጣት የሚሰራበት መሆኑን በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡