የሰላም ማስከበር ስልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

73
አዲስ አበባ ግንቦት13/2010 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወታደራዊ ኃላፊዎችን ያሳተፈ የሰላም ማስከበር ስልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ስልጠናው የውይይትና ድርድር እንዲሁም ወታደራዊ ታዛቢነት ላይ ባተኮሩ ሁለት ኮርሶች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ  ከብሩንዲ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ የተውጣጡ ወታደራዊ ኃላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው። ከአፍሪካ ህብረትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴራልና አዲስ አበባ ፖሊስ የተውጣጡ አካላትም በስልጠናው ይካፈላሉ። በሁለቱም ኮርሶች ሁለት ሳምንት የሚቆይ የንድፈ ሃሳብ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ ወታደራዊ ታዛቢነት ተጨማሪ አንድ ሳምንት የመስክ ልምምድ እንደሚደረግበት የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ዋና መምሪያ አስታውቋል። በመምሪያው የዓለምአቀፍ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የወታደራዊ ታዛቢዎችና የስታፍ መኮንኖች የስልጠና ክፍል ኃላፊ ኮሎኔል ታምራት አንዳርጌ እንዳሉት፤ የወታደራዊ ታዛቢነት ስልጠና ለተልዕኮ ለሚሰማሩ ከፍተኛ ወታደራዊ አካላት ይሰጣል። የውይይትና ድርድር ስልጠና ደግሞ ከወታደራዊ አካላት በተጨማሪ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ለሚሰማሩ የፖሊስና የሲቪል አካላት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሰራር ስርዓት መሰረት ለሰላም ማስከበር የሚሰማሩ አካላትን ክህሎት ማጎልበት የስልጠናው ዋና ዓላማ ነው። ስልጠናው በማዕከሉ ባሉ አሰልጣኞችና ከተለያዩ ተቋማት በሚጋበዙ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ኮሎኔል ታምራት ገልጸዋል። እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች በኢትዮጵያ መዘጋጀታቸው አገሪቱ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለምታበረክተው አስተዋጽኦ ልምድ እንድትቀስም ያስችላታል።  የዴንማርክ መንግስት የወታደራዊ ታዛቢነት ስልጠና ወጪን እንደሚሸፍንና የውይይትና ድርድር ስልጠና ደግሞ ከጃፓን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።  ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1951 በኮሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን አሀዱ ብላ በመጀመር በአፍሪካ ቀዳሚዋ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሳተፈች አገር መሆን ችላለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም