ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ የሚታየውን አለመግባባት ለማስወገድ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት መጀመሩ ተገለፀ።

64
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 ከአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ የሚታየውን አለመግባባት ለማስወገድ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት መጀመሩ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ የዘንደሮውን የሰንደቅ ዓላማ በዓል አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው። በዚሁ ጊዜ እንደተመለከተው 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ በዓል  "ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባም  እየተከበረ ይገኛል። በመጪው ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም በዓሉ በሁሉም ተቋማት ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብና የመስቀል ስነ-ስርዓትን በማከናወን ይከበራል ተብሏል። በከተማ ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ውይይት መጀመሩንና ውይይቱም ሁሉንም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያሳትፍ እንደሚሆን አፈ ጉባኤዋ አመልክተዋል። አፈ-ጉባኤዋ በመግለጫቸው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የረጅም ዓመታት ታሪክ ባለቤትና የነጻነት ተምሳሌት አገር ናት። ለዚሁ ለሰንድቅ ዓላማዋ ትኩረት በመስጠት በየዓመቱ ክብረ በዓል በማዘጋጀት ስታከብር ቆይታለች ብለዋል። የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበርም አገሪቱ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ውስጥ ሆና መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል በማለት ገልፀዋል። በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ እንደሚገኝ የገለጹት አፈ ጉባኤዋ ከሰንደቅ ዓላማው ጋር በተያያዘ የሚካሄደው ውይይትም አገራዊና ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ውይይቶቹ ህብረተሰቡ ስለሰንደቅ ዓላማ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረውም ያስችላል ሲሉ አፈ ጉባኤዋ ገልፀዋል። በሰንደቅ ዓላማው ማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ ዜጎች በህገ መንግስቱ የሚታወቀውን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ማክበር እንዲችሉ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከሃገር ሽማግሌዎች፣ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና  ከወጣቶች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥሩ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ማንኛውም ግለሰብ ይወክለኛል የሚለውን አርማ መያዝ እንደሚችል መግለጹን ያስታወሱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች በዓሉ በሚከበርበት የመንግስትና የግል ተቋማት ህጋዊውን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ያሉት ውይይቶችን ተከትሎም "ሰንደቅ ዓላማው ይቀየር ወይስ አይቀየር" በሚለው ሀሳብ ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ ሂደት መሰረት ያደረገ ውሳኔ በመንግስት ይሰጣል ተብሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም