የአሶሳ ከተማ ጸጥታ ወደ ቀድሞው መረጋጋት እየተመለሰ ነው– ነዋሪዎቹ

1246

አሶሳ ጥቅምት 2/2011 የአሶሳ ከተማ ጸጥታ ወደ ቀድሞው መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለጹ።

ምንጩ ያልታወቀ ሐሰተኛ ወሬ በግብይትና  እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ፖሊስ በሐሰተኛ ወሬና በሌሎች ወንጀሎች በተጠረጠሩ 41 ሰዎች ላይ ክስ መስርቼያለሁ ብሏል፡፡

ሰኔ 2010 በአሶሳ ከተማ በተከሰተ ግጭት በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የከተማዋ የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቶ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነባት ይገኛል፡፡ይሁንና በየጊዜው የሚናፈሰው ምንጩ ያልታወቀ ሃሰተኛ ወሬ በግብይት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው።

ከነዋሪዎቹ መካከል በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራችው ወጣት በላይነሽ ሺበሺ እንደተናገረችው በከተማዋ የነበረው የጸጥታ ችግር ተወግዶ ግብይት ሂደት በተለመደው መንገድ እየተካሄደ ነው፡፡

ይሁንና “ በከተማው ግጭት ሊነሳ ነው ” በሚል በየጊዜው የሚናፈሱ ሃሰተኛ ወሬዎች ተከትሎ ወደ ግብይት የሚመጣው ሕዝብ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ትናገራለች፡፡

ይህም በግብይት ወቅት አለመረጋጋት በመፍጠር የሸማቹንም ሆነ ነጋዴውን ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ያውካል ብላለች፡፡

አንዳንድ ነጋዴዎችም አጋጣሚውን ተጠቅመው ዋጋ ለመጨመር እንደሚሞክሩ ወጣት በላይነሽ ትናገራለች፡፡

አቶ አብዱራሂም መሐመድ የተባሉ ነዋሪ ደግሞ ሃሰተኛ ወሬው የኅብረተቡን መቻቻል ለማደፍረስ የሚፈልጉ አካላት የፈጠሩት ሳይሆን እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡

አሁን ያለው አንጻራዊ የከተማው ሰላም በኅብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ጥረት መገኘቱን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የከተማውን ጸጥታ ለማሻሻል የመቻቻል ባህሉን ማስቀጠል ወሳኝ እንደሆነ መክለዋል፡፡

ችግሩን ለማስወገድ አስተዳደሩና ኅብረተሰቡ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አኑር ሙስጠፋ ሐሰተኛ ወሬን ጨምሮ ወንጀልን በመከላከል በከተማው ሠላም ለማስፈን የተደረገውን ጥረት ይናገራሉ፡፡

እንደ ኃላፊው  ገለጻ በከተማው በተለይ በምሽት ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦች ዋነኛ ቦታዎች ተለይተው እየተሰራባቸው ነው፡፡

የከተማው ነዋሪዎች ተሸከርካሪዎቻቸውን ከመስጠት ጀምሮ የጸጥታ ሥራውን አጋርነቱን በተግባር እያሳየ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ኅብረተሰቡን በሃሰተኛ ወሬ ለማሸበር የሞከሩትን ጨምሮ በዘረፋ ፣ድብደባና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 41 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሚጠቀሙባቸው ዘጠኝ ሸጉጦች፣ ገጀራዎች፣የበር ቁልፎችና መፈንቀያዎች፣ ከጸጥታ ኃይሎች  ተመሳስለው የተሰፉ የደንብ ልብሶች እንዲሁም የዘረፏቸው ቴሌቪዥኖችና ሌሎችም ቁሳቁስ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ከኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች ከተሞች እስከ 300 ሺህ ብር ዘርፈው በከተማው የተሸሸጉ ሁለት ተጠርጣሪዎች ከማስረጃ ጋር ለክልሎቹ ተላልፈው መሰጠታቸውን አብራርተዋል፡፡

ከከተማው መስፋት ጋር ተያይዞ የፖሊስን አደረጃጀት በማስተካከል የኅብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከ50 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት ይገመታል፡፡