በቢሾፍቱ ከተማ የክትባት ማምረቻ ተመረቀ

1700

አዳማ ጥቅምት 1/2011 የበጎችና ፍየሎችን ደስታ መሰል በሽታን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት በቢሾፍቱ ከተማ በ23 ሚሊዮን ብር የተደራጀው የክትባት ማምረቻ ዛሬ ተመረቀ።

የክትባት ማምረቻ ቴክኖሎጂው የተቋቋመው ከዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሃንስና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ተወካይ ሚስተር ዶሚኒክ ዳቮክስ  በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ውስጥ የተገነባውን የክትባት ማምረቻ ቴክኖሎጂ መርቀው ከፍተዋል።

ዶክተር  ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሃንስና በምረቃ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት  የክትባት ማምረቻው ደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች በሽታን እ.ኤ.አ እስከ 2027  ከአገሪቱ ለማጥፋት እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ለማሳካት ወሳኝ ነው፡፡

ከአሁን በፊት የሚመረቱ ክትባቶች የቅዝቃዜ ሰንሰለቱ ተጠብቆ እንስሳቱ በሚገኙባቸው ቆላማ አካባቢዎች አንቀሳቅሶ  ክትባቱን ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ቴክኖሎጂው የነበረውን ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ “ቴርሞስተብል” የተባለ ክትባት ለማምረት የሚያስችልና ክትባቱም የትም ቦታ ቢሄድ ማቀዝቀዣ የማይፈልግ በመሆኑ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የክትባቱን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለማጥፋት አገራዊ ስትራቴጂ ተቀርፆ ስራ ውስጥ ከተገባ ሁለት ዓመት ማስቆጠሩን ያመለከቱት ዶክተር ገብረእግዚአብሔር በተለይ አርብቶ አደር በሆኑት የአፋርና ሶማሌ ክልሎች ሰፊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው።

ለሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑና ጥምር ግብርና በሚካሄድባቸው ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልሎችም በጎችና ፍየሎች በበሽታው የመጠቃት፣የመሞት ሁኔታን የመቀነስና በዘላቂነት ለማጥፋት የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች አደገኛ በሽታን የመቆጣጠርና የማጥፋቱ እንቅስቃሴ በቅርቡ በ170 ሚሊዮን ዶላር ይፋ የተደረገው የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ፕሮጀክት አካል ነው።

የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ማርታ ያሚ የክትባት ማምረቻ ቴክኖሎጂው ሙቀትን የሚቋቋም ክትባት ለማምረት የሚያስችል በመሆኑ ዘመናዊና ተመራጭ ነው።

ኢንስቲትዩቱ በ2011 ዓ.ም 55 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በማምረት ለአገር ወስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ማርታ 22 ዓይነት 250 ሚሊዮን ዶዝ ክትባቶችን በዓመት የማምረት አቅም መገንባቱንም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ተወካይ ሚስተር ዶሚኒክ ዳቮክስ በበኩላቸው የክትባት ማምረቻ ቴክኖሎጂው ከአገሪቱ ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር ስጋት ተኮር የክትባት ዘመቻ ለማከናወን ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡