የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትና የተቋሙ ሠራተኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

2180

ነቀምቴ ጥቅምት 1/2011 የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትና የተቋሙ የነቀምቴ ካምፓስ ሠራተኞች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

ባለሀብቱና ሠራተኞች ድጋፍ ያደረጉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው።

ከአንድ ሚሊዮን 151 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፉን በመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች ያስረከቡት የዩኒቨርሲቲው ነቀምቴ ካምፓስ ዲንና የባለሀብቱ ተወካይ አቶ ወንድሙ ቀኖ ናቸው፡፡

ተወካዩ ድጋፉን ዛሬ ለምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት የተደረገው እርዳታ ብርድ ልብስ፣ አልባሳት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና የተለያዩ የሕጻናት ምግቦችን ያካተተ ነው፡፡

” እርዳታው የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ” ያሉት አቶ ወንድሙ ተፈናቃዮቹ መልሰው እስኪቋቋሙ ድርስ በባለሀብቱ በኩል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው እርዳታውን ሲረከቡ እንደገለጹት ተፈናቃዮቹ ከመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አካላት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

ባለሀብቶች፣ ቄሮዎች፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የክልሉ መንግስት ከፌዴራል አካላት ጋር በመተባበር ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ሌት ተቀን እየሰሩ ያሉትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትና ሠራተኞች ለተፈናቃዮች ባደረጉት ድጋፍ በራሳቸውና በምስራቅ ወለጋ ዞን ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን በበኩላቸው ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቶች፣ ቄሮዎችና መንግስታዊ ተቋማት ከመጀመሪያ ጀምሮ እያደረጉት ላለው ድጋፍና እገዛ በራሳቸውና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስም መስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል በዛሬው ዕለት ያደረገው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ተፈናቃዮች ወደቄያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ባለሀብቶች፣ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡