የኢትዮ-ህንድ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል ሊቋቋም ነው

71
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 የኢትዮ-ህንድ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል ከአንድ ወር በኋላ ስራ እንደሚጀምር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ። በሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ካሊድ አህመድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ማዕክሉ ከህንድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚቋቋም ነው። ተቋሙ አገሪቱ የምትፈልጋቸው የተመረጡ ቴክኖሎጂዎች ህንድ አገር ተሞክረው ውጤታማ የሆኑትን በማምጣት የማላመድና ወደ ገበያ የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በህንድ የአቅም ግንባታ ስልጠናና በባለሙያዎች የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደረግም ገልፀዋል። የተመረጡና የተሞከሩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢትዮጵያውያንና የህንድ ባለሀብቶች በጋራ በቴክኖሎጂ ቢዝነስ ዘርፍ እንዲሰማሩ ያደርጋልም ነው ያሉት። ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የቴክኖሎጂ ፍኖተ-ካርታ መሰረት በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ መስኖ፣ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያና በሌሎችም ዘርፎች ቴክኖሎጂዎችን የማባዛት ስራ ይሰራል። በመጀመሪያው ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው የግብርና እና የመስኖ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ማዕከሉ በመጀመሪያው ዙር እስከ አምስት ዓመት እንደሚቆይ ገልፀው በዓመት በትንሹ 20 ቴክኖሎጂዎችን ለማስተላለፍ አቅዷል ብለዋል። የማዕከሉ መቋቋም ህንድ በቴክኖሎጂ የተሻለ አቅም ስላላት ለአቅም ግንባታ እና ተፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያ በኩል ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ ገልፀው ከህንድ በሚመጣ ማረጋጋጫ በአንድ ወር ውስጥ ስራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም