የኢትዮጵያና ቱኒዚያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በአዲስ አበባ የልምድ ልውውጥ አደረጉ

60
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከቱኒዚያ አቻው የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ የልምድ ልውውጥ ምክክር አድርጓል። ሁለቱ ምክር ቤቶች የንግድ አጋርነትን የሚያጠናክር የጋራ መግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል። በቱኒዚያ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተመራው በግብርና ምርት ማቀነባበርና በኢንዱስትሪ ቁሳቁስ የሚሰሩ 40 የሚደርሱ የቱኒዚያ የባለሀብቶች ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማሪያም በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በኢትዮጵያ በግብርና ምርት ማቀነባበርና በኢንዱስትሪ ቁሳቁስ ለሚሰሩ የንግድ አጋሮችና ባለሀብቶች ምቹ  ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ የመሰረተ ልማት እድገት እና የግብርና ምርት ማቀነባበር እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመበራከት ላይ መሆናቸውንም አቶ ሺበሺ ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል። በተጨማሪም መንግስት በነዚህ ዘርፍ የሚያደርገውን የግብር እፎይታ ጊዜ፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እና ሌሎች ማበረታቻዎች በመኖራቸው ያለውን መጠነ ሰፊ የሰው ኃይል ለመጠቀም የቱኒዚያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል። የቱኒዚያ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሚስተር ነጂብ ሚል በበኩላቸው በሁለቱም አገሮች የንግድ እድሎች በመኖራቸው ከቱኒዚያ የመጡት የንግድ ልዑካንም በኢትዮጵያ ያሉትን አማራጮችና አጋሮች ለመመልከት መምጣታቸውን ገልፀዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም የቱኒዚያ ኩባንያዎች በቀጣይ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክሩ የጋራ ፕሮጀክቶች የማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸውም ገልፀዋል። በሁለቱ አገሮች የንግድ ምክር ቤቶች መካከል የተደረገው የመግባቢያ ትብብር ስምምነት የኢትዮጵያና ቱኒዝያን የንግድ አጋርነት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ቱኒዚያ በንግድና ዲፕሎማሲ  ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት ቢኖራቸውም በዓመት ያላቸው አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ መጠን ግን ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመላክታሉ። ኢትዮጵያ ፍራፍሬዎችን፣ የቆዳ ውጤቶችን እና የጥጥ ምርት ወደ ቱኒዚያ የምትልክ ሲሆን ቱኒዚያ ደግሞ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን እና የነዳጅ ዘይትና ከፋብሪካ የወጡ ጨርቆችን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች። የሁለቱ ምክር ቤቶች የንግድ አጋርነት ስምምነትም በአፍሪካ በቀጣይ የሚተገበረውን የነጻ ቪዛ አሰራር የንግድ ልውውጥ መጠኑን እንደሚያሳድገውም ነው የተገለፀው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም