ፖሊስ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት መዳህኒትና ፀረ-ተባይ ኬሚካል ሲሸጥ ነበር ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለ

83
ደብረ ማርቆስ/ደብረ ብርሃን ጥቅምት 1/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን እነብሴ ሳርምድር ወረዳ የመጠቀሚያ ጊዜው ከ6 ዓመት በፊት ያለፈበትን መድኃኒትና ፀረ-ተባይ ኬሚካል ሲሸጥ ነበር ያለውን ግለሰብ መያዙን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በሰሜን ሽዋ ዞን ደግሞ በተለያዩ የንግድ ሱቆች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 11 ዓይነት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፋብሪካ ምርት ውጤቶች ተይዘው እንዲወገዱ ተደርጓል። የምስራቅ ጎጃም ዞን እነብሴ ሳርምድር ወረዳ ጽህፈት ቤት ወንጀል ምርማራ ዋና ሳጅን አበበ ደመቀ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ታርጋ ቁጥር አ.አ 4437 ዳማስ መኪና ጭኖ በድምጽ ማጉያ እየቀሰቀሰ ሲሸጥ ነው። ግለሰቡ ከደቡብ ወሎ ዞን በመነሳት በተለያዩ አካባቢዎች ጊዜቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች እየሸጠ መምጣቱን የጠቆሙት ዋና ሳጅን አበበ እንብሴ ሳር ምድር ወረዳ ሰኞ ገበያ በመሸጥ ላይ እንዳለ በኬላ ጠባቂዎችና በአካባቢው ፖሊሶች እጅ ከፈንጅ መያዝ ተችሏል፡፡ ግለሰቡ ምንም አይነት  ፈቃድ እንደሌለውም ገልፀዋል፡፡ በእለቱ የተያዘው መድሃኒት ውስጥ አንድ ካርቶን የአይጥ መርዝ፣ አንድ ካርቶን የሰው ህክምና መስጫ መርፌና 5 ሊትር ፈሳሽ ፀረ-ተባይ ኬሚካል መሆኑ ተናግረዋል። ዋና ሳጅን አበበ አክለው እንዳሉት የአይጥ መርዙና የፀረ- ተባይ ኬሚካሉ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ከ6 ዓመት በፊት ያለፈበት መሆኑ በግብርና ባለሙያዎች ማረጋገጥ ተችሏል። የህክምና መርፌም ከፀረ- ተባይ ኬሚካልና መርዝ ጋር ተደባልቆ መቀመጡ ለተለያየ የጤና ጉዳት የሚዳርግ መሆኑ በጤና ባለሙያዎች አስታያየት መሰጠቱን ዋና ሳጅን አበበ አመልክተዋል። ፖሊስ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሃኒቶችና ፀረ-ተባይ ኬሚካል ሲያዘዋውር በተያዘው ግለሰብ ላይ ምርምራ አካሂዶ ለወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ''ጉዳዩን የሚመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው'' በማለቱ ጉዳዩን ወደ ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ለመላክ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሰሜን ሽዋ ዞን በተለያዩ የንግድ ሱቆች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 11 ዓይነት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፋብሪካ ምርት ውጤቶች መያዙን በዞኑ ንግድ ኢንዲስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ የውጭ ድህረ ፍቃድ ኢንሰፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ዘነበ ክንፈ አስታውቀዋል። ከተያዙት መካከልም 9 ሺህ 372 ሊትር የተለያዩ የታሸጉ ለስላሳ መጠጦች፣ 28 ኪሎ ግራም የታሸጉ ደረቅ ምግቦች፣ 37 ሊተር ፈሳሽ ሳሙና፣ 41 ሊትር የመዋቢያ ቅባቶችና  የምግብ ጨው ይገኙበታል። በቁጥጥር ስር ውለው እንዲወገዱ የተደረጉት እነዚህም የፋብሪካ ምርት ውጤቶች 285 ሺህ 611 ብር ዋጋ ግምት ያላቸው ናቸው፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦች በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጥሩ ህብረተሰቡም ሆነ ነጋዴው ሲገዛ የመጠቀሚያ ጊዜውን አረጋግጦ መሆን እንዳለበት ቡድን መሪው ተናግረዋል። ደብረ ብርሃን  ከተማን ጨምሮ ጣርማ በር፣ መንዝ ቅያ፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ ሞጃና ወደራ፣ አንኮበር፣ ምንጃር ሸንኮራና ቀወት ወረዳዎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፋብሪካ ምርት ውጤቶች የተገኙባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም