በአማራ ክልል በ10 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር የማባዛት ስራ እየተከናወነ ነው

77
ባህር ዳር ጥቅምት 1/2011 በአማራ ክልል የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በ10 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የሰብል ዘር የማባዛት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የግብርና ቢሮ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ አግደው ሞላ እንደገለፁት በክልሉ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ፍላጎት ቢኖርም እስካሁን በክልሉ አቅም እየቀረበ ያለው ከ15 በመቶ አይበልጥም። በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በመኸር ወቅትና በመስኖ ልማት ምርጥ ዘር በማባዛት የዘር ፍላጎቱን በክልሉ አቅም ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፈው የመኸር ወቅትም 9ሺህ 667 አርሶ አደሮችን ጨምሮ በዩኒየኖችና በግል የማባዛት ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በበቆሎ፣ ቢራ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላና ሩዝን ጨምሮ 19 አይነት የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች እየተባዛ ሲሆን 200 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ዘር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የሚሰበሰበው ምርጥ ዘርም ለመስኖ ልማትና ለቀጣይ ዓመት የመኸር እርሻ የሚውል መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉን የዘር ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ከሌሎች ዘር አብዢ አካባቢዎች እንደሚያስመጣ ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የማርቁማ ቀበሌ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ በበቆሎና ስንዴ ዘር ብዜት በመሳተፍ የራሳቸውን የዘር ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። በየዓመቱ ከሚያከናውኑት የምርጥ ዘር ሽያጭ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት ቀቀባ የተባለውን የስንዴ ዘር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እያባዙ መሆናቸውን አመልክተው ከዚህም 36 ኩንታል ምርጥ ዘር አገኛለሁ ብለው እንዲጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የሚያመርቱትን ዘርም በውላቸው መሰረት በተሻለ ዋጋ ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል። በዚሁ ወረዳ የዋዝንክስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አምሳሉ ቆለጭ በዘንድሮው የመኽር ወቅት በአራት ሄክታር መሬት የበቆሎና የስንዴ ዘርን እያባዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። እየተባዛ የሚገኘው የስንዴ ዘር ቁመና በጥሩ ሁኔታ የሚገኝ በመሆኑ እስከ 210 ኩንታል ዘር እንደሚጠብቁ አመልክተዋል። የሚያገኙትን የበቆሎና የስንዴ ዘርም ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በማስረከብ ከወጭ ቀሪ ከ110 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በአንድ ሄክታር መሬት የቢራ ገብስ ዘር እያባዙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የሞሶብ ተራራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አለምነው ውቤ ናቸው። በመኽር ወቅት እያባዙት ካለው የቢራ ገብስም 36 ኩንታል ዘር ሰብስበው ለጉና ዘር ብዜት ህብረት ስራ ማህበር በማስረከብ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አስረድተዋል። ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ በ2009/2010 የምርት ዘመን በ9 ሺህ 741 ሄክታር መሬት ከተባዛው ዘር 116 ሺህ ኩንታል ተሰብስቦ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም