የዜጎችን ደህንነት ባልጠበቀ መልኩ ለስራ ወደ ውጭ አገራት የሚልኩ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

87
አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 መንግስት የዜጎችን ደህንነት ባልጠበቀ መልኩ ለስራ ስምሪት ወደ ውጭ አገራት በሚልኩ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ። ታግዶ የቆየው ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። የተጀመረው የውጭ አገር የስራ ስምሪት ወደ ኳታር፣ ዮርዳኖስና ሳዑዲ ዓረቢያ የሚደረግ ነው። በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት መንግስት የሥራ አጥነትን ችግር ለመቀነስና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ ቢሆንም ችግሩ ሊቃለል አልቻለም። በዚህ ሳቢያም ወጣቶች በተለያየ ሳቢና ገፊ ምክንያት በህገ ወጥ ደላሎች የሃሰት ስብከት ተገፋፍተው ለአስከፊ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል፤ በዚህ ሁኔታ ሄደው በተለያዩ አገራት ለጥቃትና በደል ተጋልጠው የቆዩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጠንካራ ዲፕሎማሲ ወደ አገራቸው መመለስ መቻላቸውንም አውስተዋል። ዜጎች በቅድሚያ በአገር ውስጥ ሰርቶ መክበር የሚቻልባቸውን እድሎችን ሁሉ አሟጠው መጠቀም እንደሚገባቸው ያስገነዘቡት አቶ ደመቀ ከዚህ ባለፈ ግን ህጋዊ መስመሩን በማስጠበቅ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ስርዓትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። በመንግስት በኩል የውጭ አገር የስራ ስምሪት እገዳ ተጥሎበት መቆየቱን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስራ ስምሪቱ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ስራው ዳግም መጀመሩን ገልፀዋል። መንግስት ወደ ውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎችን ለስቃይና እንግልት የሚዳርጉ ኤጀንሲዎችን ተከታትሎ እርምጃ እንደሚወስድም  በአፅንኦት ተናግረዋል። የውጭ አገራት የስራ ስምሪቶችን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደረጉ ዜጎች ህጋዊውን መስመር ተከትለው ሊሰማሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን ጉዞ ለማስጀመር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። በሚኒስቴሩ የስራ ስምሪት የሚያስተባብር አዲስ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙንና አደረጃጀቱም በፌደራል፣ በክልልና ዞኖች ድረስ መዋቀሩን ያብራሩት ሚኒስትሯ ለስራ የሚሄዱ ዜጎችም የብቃት ማረጋጋጫ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። በሶስት የሙያ መስኮች ከ60 በላይ ስልጠና የሚሰጥባቸው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መለየታቸውን የገለፁት ዶክተር ሂሩት 69 የጤና ተቋማትና ከ144 በላይ የውጭ አገር ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መለየታቸውን ጠቁመዋል። በኤጀንሲዎች ላይ በተደረገ የአቋም ፍተሻ ከ90 በላይ ኤጀንሲዎች የታገዱ ሲሆን የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ ከ144 በላይ ኤጀንሲዎች ደግሞ በስራው እንዲቀጥሉ ተደርጓል። በቀጣይ ወደ ሊባኖስ፣ ኩዌት፣ ባህሬን እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የስራ ስምሪት ለማስጀመር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም