አስተዳደሩ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው - ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

65
አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ። ምክትል ከንቲባው ዛሬ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል። ከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። በውይይቱ ወቅት ወጣቶች የስራ ማጣት፣ የመስሪያ ቦታና ሼዶች፣ የወሳኝ ኩነቶችና የመታወቂያ አሰጣጥ ችግሮች እንዲሁም የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ወጣት ፎዚያ ናስር የመስሪያ ቦታ፣ የሼዶችና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉብን መንግስት ሊፈታልን ይገባል ብላለች። በቅርብ ላሉ ኃላፊዎች ችግራችንን ብንነግርም በቅርቡ ይፈታል ከማለት ውጭ ያመጡልን መፍትሄ የለም ነው ያለችው። ወጣት ቢኒያም ከበደ በበኩሉ የመልካም አስተዳደር ችግር አለብን፣ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እየተፈታልን አይደለም ጥያቄዎቻችንን ለሚመለከተው አካል ብናቀርብም ምላሽ እያገኘን አይደለም ብሏል። በጥቃቅንና አነስተኛ ብንደራጅም በአግባቡ ስራ አላገኘንም ያለው ወጣት አስረስ ጌታነህ ደግሞ መንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል። ሼዶች በማን እንደተያዙ በማጣራት ላይ ነን፣ የማጣራቱ ስራ ሲጠናቀቅ ለሚመለከታቸው ሰዎች ይተላለፋሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው የሼዶችን ጉዳይ በማጣራቱ ስራ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል። ስለ መኖሪያ ቤት ለተነሳው ጥያቄም በከተማዋ የማጣራት ስራ በመስራት ለደሃ ደሃ የህብረተሰብ ክፍሎች የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ሼዶች፣ የቀበሌ ቤቶች፣ ሱቆችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለህብረተሰቡ ሲተላለፉ በግልጽ ነዋሪውን በማሳተፍ ለተገቢው ሰው ይተላለፋሉ ሲሉም አክለዋል። የመልሶ ማልማት ስራም ዜጎችን ሳያፈናቅል በያሉበት የሚከናወን ይሆናል፣ የግብር አሰባሰብን ፍትሃዊ የማድረግና ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው። ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ የዛሬውን ጨምሮ ከስድስት ክፍለ ከተሞች ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም