የአንቡላንሶችን ተደራሽነት አንድ ለ25 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ነው-ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

101
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የአንቡላንስ ተሽከርካሪዎች አንድ ለ25 ሺህ ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራሁ ነኝ ሲል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በ2010 ዓ.ም ወደ ሥራ መገባቱን  ጠቁሟል። በዚህም 3 ሺህ 14 አንቡላንሶችን ለመግዛት ታቅዶ እስካሁን 1 ሺህ 153 ግዥ ሲፈፅም የተቀሩትም የውጭ ምንዛሬ ሲገኝ ተገዝተው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥረት እንደሚያደርግ በሚኒስቴሩ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ እስክንድር ላቀው ገልጸዋል። በዘጠኙ ክልሎች፣ ሁለት ከተማ አስተዳደሮችና በዩኒቨርስቲዎች ባሉ ሆስፒታሎች አንድ አንድ አንቡላንስ ሲገዙ ጤና ጥበቃ በበኩሉ አንድ አንቡላንስ በተጨማሪነት ስለሚገዛ በአጠቃላይ ግማሹ ወጪ በሚኒስቴሩ የሚሸፈን ነው ብለዋል። የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ድንገተኛ አደጋዎች የሚከሰትን ሞትና የአካል ጉዳት ለማስቀረት ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ የህሙማንን የቅብብሎሽ ህክምና ስርዓት ለመዘርጋት በቂ አንቡላንሶች እንዲሟሉ ማድረግ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሚኒስቴሩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ለበርካታ የእናቶች ሞት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም አለመድረስና በሰለጠነ ባለሙያ አለመታየት በመሆኑ አንቡላንሶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ በተገቢው ቦታ ሊያገለግሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። በመሆኑም በአንዳንድ ክልሎች፣ ከተሞች፣ ዞንና ወረዳዎች አንቡላንሶች ከታለመላቸው ውጭ በሆነ መንገድ ለሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት መዋልና ወንበራቸው ወጥቶ ለቢሮ ወንበር መጠቀምና አንቡላንሶቹን በመቀየር ለሌላ ሥራ ማዋል ሲሆን ይህም ከህግና አግባቡ ውጭ በመሆኑ በየደረጃው ያለው አመራር ይህን በሚፈፅሙ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱም አሳስበዋል። እስካሁን አንቡላንሶችን ከታለመላቸው ቦታና ዓላማ ውጭ ሲገለገሉ የተገኙ ሰዎችና አመራሮች ሚኒስቴሩ እስከማባረርና ሌሎች የቅጣት እርምጃዎች እስከመውሰድ መድረሱን ገልጸው ህብረተሰቡና ሚድያው በጋራ ይህን ዓይነት ድርጊት በማጋለጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል። ከዚሁ በተጨማሪ አመራሮቹ በባለሙያዎች በመታገዝ፣ በጀት በመመደብና በተገቢው ጥገናና አያያዝ ሥርዓት በመታገዝ የአንቡላንሶቹ የአገልግሎት ዕድሜን የማርዘም ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አቶ እስክንድር መልእክት አስተላልፈዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በድንገተኛ አደጋ ይሁን የእናቶችና ሌሎች ህመሞች በሚከሰቱበት ወቅት ህብረተሰቡ በ0937939393/0937949494 ሞባይል ቁጥር በመደወል የአንቡላንስ አገልግሎት ማግኘት ይችላል ። በአገሪቷ እስከ 2010ዓ.ም 1ሺህ 337 አንቡላንሶች በሚኒስቴሩ ተገዝተው መከፋፈላቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም