የአእምሮ ጤና ግንዛቤን ለማሳደግ የህብረተሰቡና የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ ያስፈልጋል

97
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የአእምሮ ጤና ግንዛቤን ለማሳደግ የህብረተሰቡና የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ ተጠየቀ። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 10 በየዓመቱ የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ተብሎ ይከበራል። ይህ ዕለት ዘንድሮም “ወጣቶችና የአእምሮ ጤና እየተለወጠ ባለ ዓለም ውስጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚከበረው። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለው በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤና ችግር እየጨመረ ቢሆንም ችግሩን በተመለከተ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ግን እያደገ አይደለም። እንደ ዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ ከአእምሮ ጤና ህመም አይነቶች 50 ከመቶ የሚሆኑት የሚከሰቱት በ14 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ነው። ሆኖም በህመሙ ከተጠቁት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህመሙ እንዳለባቸው ሳይታወቅና ሳይታከሙ ቀርተው ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የአገሪቷን የጤና ፖሊሲ መነሻ በማድረግ የአእምሮ ጤና ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀትና የትኩረት መስኮችን በመለየት ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ነው። የአእምሮ ጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት አሃድ ከእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ ሁለት ሁለት ጤና ባለሙያዎች የአጭር ጊዜ የአእምሮ ጤና ስልጠና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግና ችግር ያለባቸውን ሰዎች የአእምሮ ጤና አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር የማገናኘት፣ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ ሥራ እየተሰራ ይገኛል። ሆኖም በአፈጻጸሙ ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል መልቀቅና አለመኖር፣ የግብዓት እጥረት፣ የክትትል ክፍተት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂክ ዕቅድና የትምህርት ቤት ጤናና ሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ውስጥ የአእምሮ ጤና እንደ አንድ ፓኬጅ ተካቶ ለትምህርት ቤቶች የማህበረሰብ አባላት የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል። ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በወጣቶች ስብእና፣ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችና ከሱስ ጋር በተያያዘ የ5 ዓመት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑንና በ6 ክልሎች በጤና ተቋማት የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። ያም ሆኖ የአእምሮ ጤና ግንዛቤን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት በተጨማሪ የህብረተሰቡ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ህይወት አመልክተዋል። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1992 ዓ.ም ጀምሮ መከበር የጀመረው የአእምሮ ጤና ቀን በዓለምና በኢትዮጵያም ለ26 ጊዜ ነው የተከበረው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም