በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የተደረሱ ስምምነቶች ለመተግበር በሁለቱም ወገን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል

127
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ በሁለቱም ወገን አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ገለጹ። አምባሳደሩ የተመራ የልዑካን ቡድን በፖርት ሱዳን ጉብኝት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። የልዑካን ቡድኑ ከቀይ ባህር ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኤል ሀዲ ሞሀመድ አሊ ጋር በሁለቱ አገሮች መካከል የተሟላ የኢኮኖሚ ውህደት ለማጠናከር እንዲሁም የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። ፖርት ሱዳን ለምዕራቡ የአገራችን ክፍል ካለው ቅርበት አንፃር የቁም እንስሳትን ጨምሮ ለተለያዩ የአገራችን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ የሚከናወንበትን ሁኔታ ማጥናት እንደሚያስፈልግ አምባሳደሩ ተናግረዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን ለመትግበር ከሁለቱም ወገን አስፈላጊው ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የቀይ ባህር ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኤል ሀዲ ሞሀመድ አሊ በበኩላቸው ፖርት ሱዳን የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደዚያው በረራ እንዲጀምር ጥሪ አቅርበዋል። ፖርት ሱዳን በከተማ ፕላኒንግ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም