በምእራብ ሸዋ ዞን ከ100 ሺህ በላይ ሕፃናት የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆኑ

57
አምቦ መስከረም 29/2011 በምእራብ ሸዋ ዞን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ100 ሺህ በላይ ሕፃናት የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት መረጃ ባለሙያ አቶ ባይሳ በቃና ለኢዜአ እንደገለጹት ህፃናቱ በተያዘው ዓመት የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሆኑት በዞኑ ባሉት 872 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው። ሕጻናቱን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት በዞኑ በሚገኙ 22 ወረዳዎችና ቀበሌዎች  የቤት ለቤት ምዝገባ ተካሄዷል። ሕብረተሰቡ የትምህርትን ጠቀሜታነት እየተረዳ በመምጣቱና የግንዛቤ ትምህርትና  ቅስቀሳ መሰጠቱ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲሄዱ እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ በቤት ለቤት አሰሳ የተመዘገቡት ህጻናት ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ38 ሺህ 500 ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ባሉት 872 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲስ ተመዝጋቢዎችን ጨምሮ 500 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል፡፡ እንዲሁም በዞኑ በሚገኙ 84 ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ  ትምህርት ቤቶች  45 ሺህ 414 ተማሪዎች ተመዝግበው መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ ከመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር ጎን ለጎን በተለያየ ምክንያት የትምህርት እድል ያላገኙ  118 ሺህ 766 ሕጻናትና ጎልማሶችን የመሠረታዊ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ከአንድ ሺህ 900 በላይ አዲስ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችም የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምዝገባ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የዓመቱን እቅድ  ለማሳካትና ባለድርሻ አካላት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ መምህራንና የተማሪ ወላጆች ብዙ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ደግሞ የምእራብ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ኃይለጊዮርጊስ ናቸው፡፡ የጥራትና የለውጥ ሂደቱን ለማሳካትም የአምቦ ከተማን ጨምሮ በዞኑ 22 ወረዳዎች ለሚገኙ አንድ ሺህ 168 ለሚሆኑ ርዕሰ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም ተናግረዋል። ይህም ሠላማዊ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማጠናከር እያገዘ መሆኑንም  ተመልክቷል፡፡ የአምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ዳንኤል ሙሊሳ  ለትምህርት ዘመኑ ዓመታዊ የትምህርት ዕቅድ በማዘጋጀት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሊበን መጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ተማሪ ሜቲ በየነ  በበኩሏ በዚህ አመት ከሌላው ጊዜ በተሻለ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ  መዘጋጀቷን ገልፃለች፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በትምህርት ዘመኑ ከ600 ሺህ በላይ ነባር የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል። በዞኑ በሚገኙ 22 ወረዳዎች 872 አንደኛ ደረጃና 84 የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም