የአጋር ድርጅቶች የግንባሩ አባል መሆን በአገራዊ አቅጣጫዎች የጋራ አስተሳሳብና አመለካከት ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ

79
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ እንዲወከሉ መወሰኑ በአገሪቷ ሁለንተናዊ ጉዳዮች የጋራ አስተሳሳብና አመለካከት ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ። ኢህአዴግ ሰሞኑን ባካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው አጋር ድርጅቶች ከዚህ ዓመት ጀምሮ በግንባሩ ምክር ቤት እንዲወከሉ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህ መሰረት የአጋር ድርጅቶቹ ያለ ድምጽ አስተያየትና ገንቢ ሐሳቦችን በመስጠት ልምድ እንዲወስዱ ይደረጋል። በቀጣይም አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ የድርጅቱ አባል የሚሆኑበት መንገድ ላይ ጥናት እንደሚካሄድ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ መገለጹም ይታወሳል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢህአዴግ ባካሄድው ጉባኤው ላይ አጋር ድርጅቶቹ በምክር ቤቱ እንዲወከሉ በማድረጉ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። ታዳጊ ክልሎች በአገሪቷ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ውሳኔ መሆኑንም አመልክተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ መሃመድ ቦልኮ መሃመድ እንዳሉት 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ወትሮ ካካሄዳቸው ለየት የሚያደርገው በተለያዩ መድረኮች ስንጠይቀው የነበረው የአጋር ድርጅቶች በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ተሳታፊ የማድረግ ጉዳይ መልስ የተሰጠበት በመሆኑ ነው፡፡ የአጋር ድርጅቶች የግንባሩ አባል መሆን  እና በአገሪቱ ፖለቲካ  በወሳኝነት መምጣታቸው ያላቸውን ልምድና ክህሎት ለአገሪቱ ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ስንዴ አተቤ በበኩላቸው ውሳኔው አጋር ድርጅቶች የመንግስት  አካሄድ እንዲረዱ እና  ፍትሃዊነት  ማረጋገጥ ያስቻለ በመሆኑ  በጉባኤው የተቀመጠው አቅጣጫ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ እንዲወከሉ የተላለፈው ውሳኔ ወደ ኋላ የቀሩትን ክልሎችና የመልካም አሰተዳደር ችግሮች በስፋት የሚስተዋሉባቸው አከባቢዎች ለመፍታት ከኢህዴግ ጋር በመሆን ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ክልሎቹ የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው ያደርጋል ያሉት ደግሞ አቶ ዮሃንስ ካሳሁን። የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የግንባሩ አባል መሆን ለተጀመረው አገራዊ አንድነት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጭምር ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት። የሶማሌ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ /ሶዴፓ/፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቤጉህዴፓ/፣ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/፣ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ /ሀብሊ/ እና የጋምቤላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህዴን/ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ናቸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም