በፑንትላድና በሶማሊላንድ የተከሰተው " ሳጋር " አውሎ ንፋስ የሶማሌ ክልልን ሊያጠቃ ይችላል....የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

77
ጅግጅጋ ግንቦት 12/2010 በጎረቤት ሶማሊያና የመን አገራት መካከል በሚገኘው የውቅያኖስ ባሕር የተነሳ የትሮፒካል አውሎ ንፋስ በፑንትላድ እና ሶማሊላንድ አካባቢዎች ከሦስት ቀናት ወዲህ የጎርፍ  አደጋና የሰዎችን መፈናቀል ማስከተሉ ተገለጸ፡፡ "ሳጋር" ተብሎ የሚጠረው ይህ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎችን ሊያጠቃ እንደሚችልም የሚትዎሮሎጂ ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ኃይለማርያም ለኢዜአ እንደተናገሩት በሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢ የሚገኙ ጋሻሙ፣ ደሮር እና አውበሬ ወረዳዎች በአውሎ ንፋሱ የመጠቃት አጋጣሚ አላቸው፡፡ "ሳጋር"  አውሎ ንፋስ ከፍተኛ ዝናብ የቀላቀለና በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ንፋስ ያለው በመሆኑ ይጠቃሉ በተባሉ አካባቢዎች ያሉ የሶማሌ ክልል አርብቶ አደሮች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ ሕብረተሰቡ ከወንዞች አካባቢ በመራቅና በአንድ ቦታ በመሰባሰብ ሊከተል የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ እንዲከላከልም አቶ ዘሪሁን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ የሥራ ሂዳት መሪ አቶ አብዲራዛቅ አህመድ በበኩላቸው አውሎ ንፋሱ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በሶማሌ ክልል በዓይሻ ወረዳ ደየሕ ቀበሌ 215 መኖሪያ ቤቶችን ከማፍረስ ባለፈ ለአንድ ሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በሀዲጋላ እና በደንበል ወረዳዎች በሚገኙ ገቤ እና ዶሬ ቀበሌዎች የሚገኙ 350 መኖሪያ ቤቶች በንፋሱ የመፍራስ አደጋ እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡ ንፋሱ በአካባቢዎች እያስከከተለ ያለውን ጉዳት የሚያጣሩ ከክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ዘጠኝ ባለሙያዎች ወደ ጠረፋማ የክልሉ አከባቢዎች መላካቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ የጤና ባለሙያዎችን የያዙ ዘጠኝ አምቡላንሶች ወደስፍራው ዛሬ ጠዋት መንቀሳቀሳቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም