ለአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ ገበሬዎች በበሬ ዋጋ ዘመናዊ ማረሻ ሊቀርብ ነው

108
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ ገበሬዎች በሬን የሚተካ ተራማጅ ማረሻ ይፋ ሊያደርግ ነው። ቴክኖሎጂው የኢትዮጵያን ገበሬ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና እርፍ ጨብጦ የመሄድ ያህል በቀላሉ  ሊገለገሉበት የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል። በኢትዮጵያ ግብርናውን ለማዘመን እየተሰሩ ካሉ ዘመናዊ አሰራሮች መካከል መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የተራማጅ ትራክተሩ ዋጋ ከበሬ ዋጋ ባነሰ እንደሚቀርብም ነው የተነገረው። ከቀናት በኋላ ይፋ የሚደረገው ይህ ዘመናዊ ማረሻ ከሞተሩ በስተቀር ዲዛይን ተደርጎ የተመረተው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በአገር ውስጥ የተመረተ ነው። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው በሬን ተክቶ ማረስ የሚችል ዘመናዊ መሳሪያ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ሜካናይዜሽን አሰራር እየሄደች ቢሆንም አብዛኛው ገበሬ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ባለቤት በመሆኑ በዚህ ውስጥ የመጠቃለል እድሉ አነስተኛ ነውም ብለዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ አነስተኛ ማሳ ያላቸው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከበሬ የአስተራረስ ዘዴ ወጥተው ዘመናዊ አስተራረስን እንዲከተሉ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ እንደሆነም ይናገራሉ። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ለአጠቃቀም ምቹ ተደርጎ የተሰራው ዘመናዊ ማረሻው በበሬ ትከሻ ሲያርሱ ለነበሩ ገበሬዎች ድካምን በመቀነስና ምርታማነትን በመጨመር የላቀ ጠቀሜታ አለው። ኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ በግብርና የሚተዳደር ከመሆኑ አንጻር በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የግብርና ስራቸውን በበሬ ትከሻ ያከናውናሉ። በዚህም ምርታማነትን በማሻሻል እራሱን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ከ100 ሚሊዮን በላይ የደረሰውን ህዝብ ለመመገብ ሲቸገር ይስተዋላል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለአነስተኛ ማሳ ባለቤት ገበሬዎች በዋጋና በአጠቃቀም ተስማሚ ነው ያለውን ዘመናዊ ማረሻ ወደ ስራ ሲያስገባ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ታስቦ ነው። ዘመናዊ ማረሻውን ለሁሉም አርሶ አደር ለማዳረስም የመንግስት፣ የግል እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ተቋማት ሊረባረቡ እንደሚገባም ገልጸዋል። ትራክተሩ የሚሰራው በነዳጅ ሲሆን በሂደት በጸሃይ ሃይል ቻርጅ በሚደረግ ባትሪ የሚሰራ ይሆናል ተብሏል። ትራክተሩ ሞተርና ማረሻ ያለው ሲሆን ገበሬው በበሬ ሲያርስ እርፍ እንደሚይዘው በትራክተሩም በተመሳሳይ የሚሰራ ይሆናል። የኢትዮጵያ ገበሬ ለበርካታ ዓመታት በበሬ እያረሰ ስራው አድካሚ ከመሆኑ ባለፈ የሚያመርተው ምርትም የድካሙን ያህል የሚያረካ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። በቀጣይም የሰብል ማጨጃን ጨምሮ ሌሎች አሰራርን የሚያቀሉና ምርትና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይፋ እንደሚደረጉም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም