ኅብረተሰቡ ቁጠባን ባህሉ እንዲያደርገው የ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' አሸናፊዎች ተናገሩ

82
ድሬዳዋ መስከረም 28/2011 ኅብረተሰቡ ቁጠባ ራስንና አገርን መለወጫ አማራጭ መሆኑን  በመረዳት  ባህሉ እንዲያደርገው የ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' አሸናፊዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰባተኛ ዙር የ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' መርሃ ግብር አሸናፊዎች በድሬዳዋ የሚኒባስ መኪናና ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ሽልማቶችን ለደንበኞቹ አበርክቷል፡፡ ተሸላሚዎቹ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ቁጠባ ሕይወትን ለመለወጥ ያለውን ሚና በመረዳት መልመድና መተግበር ያስፈልጋል። የጎዴ ከተማ ነዋሪና የጤና ባለሙያ ናትናኤል ሁነኛው''መቆጠብ የራሴን ህይወት በእጅጉ ለውጦታል። እኔ በቆጠብኩት ጭምር ደግሞ የኢንቨስትመንት ሥራዎችና ልማት እንደሚጎለብቱ እረዳለሁ'' ብሏል፡፡ የሚኒባስ ተሸላሚ ያደረጋቸውን ቁጠባ ከጀመሩ 16 ወራት እንደሆናቸው በመጠቆም፡፡ የባለሦስት እግር ታክሲ ተሸላሚ አቶ ተስፋዬ ገብሩ ቁጠባ የክፉ ቀን ደራሽ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሙኝን የህይወት ችግሮች ያቃለለኩት በቆጠብሁት ገንዘብ ነው ብለዋል፡፡ የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ተሸላሚው ወጣት ታሪኩ ማስረሻ ''እኔ መቆጠብ ከጀመርሁ ወዲህ ነው። የነበረኝን የገንዘብ እጥረትና ብክነት የተፈታው። ትምህርቴንም መቀጠል የቻልሁት'' በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድሬዳዋ ዲስትሪክት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤልሣቤት ገብሩ ባንኩ የጀመረው የሽልማት መርሐ ግብር የኅብረተሰቡ የቁጠባ ባህል በማሳደግ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ደንበኞች ለማፍራት እንዳስቻለው ገልጸዋል፡፡ የምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ቁጠባ ከመርሐ ግብሩ መጀመር በኋላ ዕድገት በማሳየት አሁን በ13 ቢሊዮን ብር ተቀማጭና  1ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳፈራለት ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዶክተር አዱኛ ታፈሰ ባንኩ የቁጠባ ባህል እንዲጎለብት የሚያደርገው እንቅስቃሴና በአገሪቱ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቀጣይነት እያበረከተ  ያለውን አስተዋጽኦ አበረታች ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም