የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ጉባዔ እየተካሄደ ነው

136
አዲስ አበባ መስከረም 28/2011 በኢትዮጵያ ጥንታዊ የፅሁፍ ኃብት ያለበትን ሁኔታ የመፈተሽና ጥቅም ላይ የሚውልበትን ስልት የመቀየስ ዓላማ ያለው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ጉባዔ በአዲስ አበባ ተከፈተ። "የፅሑፍ ቅርሶቻችን በምድረ ቀደምት" በሚል ርእስ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በመተባበር ያዘጋጁት የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተጋበዙ የዘርፉ ምሁራን የተሳተፉበት ጉባኤው በኢትዮጵያ ያሉ ጥንታዊ የፅሁፍ እውቀት ኃብቶች መገኛ ቦታ፣ ሊሰጡ የሚችሉትን ጥቅም፣ እየተደረገላቸው ያለውን አያያዝና መሰል ሁኔታዎች ይቃኛል። ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር የአሜሪካ፣ የጣሊያን፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የግሪክና የካናዳ ምሁራን እስከ ነገ በሚቆየው ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀርባሉ። በኢትዮጵያ ሳይንስን፣ ኢንጂነሪንግና ሕክምናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የእውቀት ኃብት ያላቸው ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ጥንታዊ ጽሁፎች እንዳሉ ይነገራል። መጠናቸው በውል የማይታወቁ በርካታ መሰል የእውቀት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ጥንታዊ የጽሁፍ ኃብቶችም በተለያዩ ውጭ አገራት አሉ ተብሎም ይታመናል። ዓለም አቀፍ ጉባኤው ኢትዮጵያ ያላትን በፅሁፍ የተቀመጠ ጥንታዊ የእውቀት ኃብት ለመለየትና ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ መቀየስ በሚቻልበት መንገድ ላይ ይመክራል ተብሏል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዘመናት ያስቆጠሩ የቃላትና የስነ-ጽሁፍ ባለቤት በመሆኗ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር አድራጊዎች ትኩረት መሳብ ችላለች። የዛሬው ጉባዔም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሁፍ ኃብት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ስነ-ጽፎቹን ለትውልድ ለማሳወቅና ግንዛቤ ለመፍጠርም ያስችላል ብለዋል። ይህም አገር በቀል እውቀቶችን በመለየትና በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ በማካተት የትምህርት ዘርፉን ጥራት ለማሳደግም የበኩሉን አስተዋጾኦ እንደሚያደርግ ነው ሚኒስትሯ የገለፁት። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጥንታዊያት መዛግብት ተባባሪ ፕሮፎሰር መርሻ አለህኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በርካታ የግዕዝ፣ የአረብኛና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ 'አጂም' የሚባል ጥንታዊ መጻህፍት ባለቤት ናት። እነዚህ መፅሀፍት በውስጣቸው ከያዙት ሃይማኖታዊ እውቀት ባሻገር የሳይንስ፣ የኢንጂነርግ፣ የሕክምናና የመሳሰሉትን እውቀቶች ለትውልዱ ለማሳወቅና ጥቅም ላይ ይውሉ ዘንድ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ መነጋገር የጉባዔው ዓላማ ነው ሲሉ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ካሉት የስነ-ጽሁፍ ኃብቶች መካከል የሚፈለጉትን እውቀቶች ለመለየትም ጉባኤው ዓይነተኛ ፋይዳ አለው በማለት ተናግረዋል። የአገሪቱን የፅሁፍ እውቀት ኃብት በአግባቡ ጠብቆ በመያዝ፤ ለአገራዊ ልማት ጥቅም የሚውልበትን ስልት መቀየስ ከጉባኤው ይጠበቃል ሲሉ በብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዬ አስታውቀዋል። በተለይም በውጭ አገራት የሚገኙ ጥንታዊ ጽሁፎች ወደ አገር ቤት የሚመለሱበትን መንገድ ለማመቻቸት ጉባኤው መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም