በፓርኮችና በዱር እንስሳት ላይ የተጋረጡትን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል እየሰራሁ ነው-ባለሥልጣኑ

64
አዳማ መስከረም 27/2011 በፓርኮችና የዱር እንስሳት ላይ የተጋረጡትን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል እየሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ። በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ትብብርና ድጋፍ በህገ መንግስቱ መርሆዎች፣በወንጀል መከላከል ፣በወታደራዊ ሳይንስና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና የወሰዱት 80 ባለሙያዎች ዛሬ ተመርቀዋል። የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኩሪያ እንደተናገሩት በአገሪቱ አዕዋፍ፣በአጥቢናብርቅዬ የዱር እንስሳት እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል የደህንነትና ፀጥታ አካላትን አቅም፣አመለካከትና ክህሎት እየገነባ ነው። በዚህም በዱር እንስሳት ላይ እየደረሰ  ያለውን ጥፋት በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል። በፌዴራልና በክልል የሚተዳደሩ ብሔራዊ ፓርኮች በሚያገጥማቸው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የዱር እንስሳት ሀብቱ እየተሰደዱ፣እየሞቱና መጠናቸው እየተመናመነ መምጣቱንም  አስረድተዋል። ህገ ወጥ አደን፣የግጦሽና እርሻ መስፋፋት፣በደን አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን ህገ ወጥ ሰፈራና የደን ውድመት በዘርፉ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውንም አቶ ሰለሞን  አስረድተዋል። የፓርኮች ደህንነት እንዲጠበቅና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ዘርፉን የደህንነትና የፀጥታ አካላትን አቅም፣አመለካከትና ክህሎት በመገንባት ላይ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እየሰጠ ላለው ድጋፍና ትብብር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የባለስልጣኑ የደህንነትና የፀጥታ ኃይል በቆይታቸውያገኙትን ዕውቀት፣ክህሎትና ግንዛቤ ለባልደረቦቻቸው ጭምር በማስገንዘብና በማስረፅ የተጋረጠውን አደጋ መቀልበስ እንደሚገባቸው የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና ናቸው። ተመራቂዎቹ ያገኙትን ሙያዊ ክህሎት በፓርኮቹ አካባቢዎች የሚኖሩትን አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በአመለካከት የሚለውጥ ግንዛቤ በማስጨበጥና የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ መሥራት እንደሚጠቅባቸው አሳስበዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ታምራት ዳባ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ የቱሪስት መስህቦች የሆኑትን የዱር እንስሳት መጠበቅና ማንከባከብና ሀብቱን ከጥፋት መከላከል የሚቻልበትን አሰራር ያካተተ ዕውቀት ማግኘታቸውን አስረድተዋል። የዱር እንስሳት መኖሪያ የሆነውን ደን በአግባቡ ማንከባከብ፣መጠበቅና ማልማት የሚቻለው ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በመሆኑም ሰልጣኞቹ ያገኙትን ሙያዊ ዕውቀት ሥራ ላይ እንዲያውሉት አስገዝበዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ከኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የመጡት አቶ ተመስገን ኮምቶ በስልጠናው ያገኙትን ሳይንሳዊ ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በአካባቢው ያለው አርብቶ አደር ማህበረሰብ በአደን ህይወታቸውን ስለሚመሩ የህገ ወጥ አደን አስከፊነትን በማስተማር አመለካከታቸውን ለመቀየር ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል። በፓርኮች አካባቢ የሚታየውን ህገ-ወጥ አደን፣ግጦሽ፣የሰፈራና የእርሻ መስፋፋትን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ ጋር ተባብራ ለመስራት የሚያስችላትን ሙያዊ ዕውቀት ማግኘቷን የገለጸችው ደግሞ ወይዘሪት ትበለጥ መለስ ናት።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም