ከምርምር ማዕከላት የሚወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

3757

ጭሮ ግንቦት 12/2010 በግብርና ምርምር ማዕከላት የሚቀርቡ የተሻሻሉ የእህል ዝርያዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የጭሮ ብሔራዊ የማሽላ ምርምርና የስልጠና ማዕከል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዳሮለቡ ወረዳ ያከናወናቸው የምርጥ ዘር ማባዛት ሥራዎች ትላንት ከክልልና ከፌደራል በመጡ ባለድርሻ አካላት ተጎብኘቷል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቲውት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በግብርና ምርምር ማዕከላት የሚቀርቡ የተሻሻሉ የእህል ዝርያዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ ናቸው፡፡

በምርምር የሚወጡ ዝርያዎች ድርቅን፣ በሽታንና ተባይን ተቋቁመው ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል ፡፡

በተደጋጋሚ በድርቅ ለሚጠቃው የሀረርጌ  አካባቢ ተስማሚ የሆነውን ” መልካም ” የተሰኘውን ምርጥ የማሽላ ዘር የአካባቢውን አርሶ አደር በተጨባጭ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ለእዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

“የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየርና ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው” ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ማዕከል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር ዶክተር አሰፋ ተኣ ናቸው፡፡

በምዕራብ ሀረርጌ ውስጥ የሚገኙ ሦስት የምርምር ማዕከላት ከተቋቋሙ አጭር ጊዜ ቢሆንም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

“አርሶ አደሩም በምርምር ማዕከላቱ የሚቀርቡትን ምርጥ ዘሮችን ብቻ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲውት የጭሮ ብሔራዊ የማሽላ ምርምርና የስልጠና ማዕከል ዳሬክተር አቶ ሞጎስ ሞኮንን በበኩላቸው ማዕከሉ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በ50 ሄክታር ላይ ምርጥ ዘርን በማባዛት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

” መልካም የተሰኘ የማሽላ ዘርን ጨምሮ ለአርሶ አደሩ የተሻለ ምርት ያስገኛሉ ተብሎ የታመነባቸውን የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በማላመድ፣ በማስተዋወቅና በማሰራጨት ላይ ይገኛልም ” ብለዋል፡፡

የማሽላ ምርጥ ዘሩ አርሶ አደሩ ምርቱ በእጥፍ እንዲጨምር የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ የቴክኖሎጂ ስርጸትና ኮሜርሻላይዜሽን ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ደራራ ሶሪ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨሪ ምርጥ ዘሩ ድርቅን መቋቋም የሚችልና በአራት ወር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ በመሆኑ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳቢተ ጠሂብ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ምርጥ ዘሮችን በሚገባ እንዲጠቀሙ በማድረግ ሕይወቱ ለማሻሻል እንደሚሰራ አመልክተዋል፡