የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና መምህራን በምሥራቅ ወለጋ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሦስት ሚሊዮን ብር ለገሱ

100
አምቦ መስከረም 27/2011 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና መምህራን በምሥራቅ ወለጋ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሦስት ሚሊዮን ብር ለገሱ ። ሁለት ተቋማትም 626ሺህ ብር ግምት ያለው ድጋፍ በዓይነትና በቁሳቁስ አድርገዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ታደሠ ቀነአ እንደገለጹት መምህራኑና ሠራተኞቹ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከልል ለተፈናቀሉት ወገኖች ድጋፉን ያደረጉት ከአንድ ወር ደሞዛቸው 30 በመቶ በመለገስ ነው ። ''ለወገን ደራሽ ወገን ነው!'' በሚል መርህ በመነሳሳት ድጋፉን ለማድረግ የወሰኑት ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና  ሠራተኞች ናቸው። በሌላ በኩል የአራረ ዋቀዮ አዱኛ ነቀምቴ ቤተክርስቲያን ለተፈናቃዮች 250 ሺህ ብር ግምት ያለው  ድጋፍ አድርጋለች። ቤተክርስቲያኗ ለተፈናቃዮቹ ያበረከተችው 200 ኩንታል ዱቄትና 260 ብርድ ልብስ  መሆኑን ወንጌላዊ መሠረት ታዬ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የምሥራቅ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው  ለተጠለሉት ወገኖች 376 ሺህ 725  ብር ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የጽህፈት ቤቱ የአደጋ ስጋት ቅነሣና  ምላሽ ሰጪ ባለሙያ አቶ ጋዲሣ ዳፊሣ አስታውቀዋል። በሳሲጋ ፣በሐሮ ሊሙ፣በበጉቶ ጊዳ፣በዲጋ ወረዳዎችና በነቀምቴ ከተማ ለተጠለሉት ተፈናቃዮች የተከፋፈለው ዱቄት፣ ብርድ ልብስ ፣የሕፃናት አልባሳት፣መድኃኒት፣ድንኳንና የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም