የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ሊፈጸም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ሊፈጸም ነው

የካቲት 24/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ሊፈጸም ነው።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ ግብይት የክፍያ ስርዓትን በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ መንግስት የነዳጅ ግብይት ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
መንግስት በነዳጅ ላይ ከግማሽ በላይ ድጎማ በማድረጉ ከዓለም አቀፍ ገበያ አንፃር የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሄም በነዳጅ ግብይቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸው ወደ ትክክለኛ ዋጋው ለመውሰድና ስርጭቱን ለማስተካከል ግብይቱን በኤሌክትሮኒክ ስርዓት ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል፡፡
እስካሁንም 1 ሺህ 26 ማደያዎች በቴሌ ብር የክፍያ ስርዓት እያከናወኑ መሆኑን አስታውሰው፤ ከቅርብ ቀናት በኋላ የነዳጅ ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፤ መንግስት የነዳጅ አቅርቦት በትራንስፖርት ዘርፍ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በርካታ እርምጃዎች መውሰዱን ገልጸዋል።
የክፍያ ስርአቱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አለመሆን በድጎማ ስርዓቱ ላይ ችግር በመፍጠሩ ለቁጥጥርም አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የነዳጅ ግብይቱን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ብቻ በመፈፀም አገልግሎቱን ማሳለጥ አስፈልጓል ብለዋል፡፡