የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 24/2015 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል አሰራሮችን ለማስፋትና ለማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር አደረገ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሰኪያጅ አንዋር ሶሳ ፈረመውታል።

 የባንኩ ፕሬዝዳት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።

 የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከአንድ ትሪሊየን መሻገሩን ገልጸው ለዚህም የዲጂታል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለስኬቱ የጎላ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

 አሁንም የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በመሆኑም ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት በባንኩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዘመናዊ አሰራር የተደገፉ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።  

ይህም የባንኩን አቅም ከማሳደግ በዘለለ የተገልጋዩንና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚረዳ አብራርተዋል። 

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንዋር ሶሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የዲጂታል ተደራሽነት እየተስፋፋ መምጣቱ የሚበረታታ ነው። 

በተለይም ''ዓለማችን በልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች አንድ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ጊዜ አማራጮችን በማስፋት ተደራሽ ማድረግ የግድ ያስፈልጋል'' ብለዋል። 

በተለይም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዲጂታል አሰራር መደገፋቸው ዘመናዊነትን ከማጉላት በዘለለ አገራዊ ፋይዳውም የጎላ ነው ብለዋል። 

በመሆኑም ሳፋሪኮም ኢትዮጰያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረገው ሥምምነት ለዲጂታላይዜሽን ትግበራ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ነው ያሉት። 

ተቋማቸው ባንኩ በዲጂታል አሰራር መስጠት የሚፈልጋቸውን የትኛውንም አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ሥራ አሰኪያጁ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም