ለኢንተርፕራይዞች ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል

አዳማ /ኢዜአ/ የካቲት 23/2015 ለኢንተርፕራይዞች ባለፉት ስድስት ወራት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን የኦሮሚያ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

 "ለኢንተርፕራይዞች ልማት ትኩረት በመስጠት በሀገር ምርት እንኩራ" በሚል መርህ የዘንድሮው የኦሮሚያ ክልል የአምራች ኢንተርፕራይዞች ባዛርና አውደርእይ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከፍቷል። 

የኦሮሚያ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ በወቅቱ እንደገለፁት ባዛርና አውደ ርእዩ በክልል ደረጃ ሲካሄድ ዘንድሮ ለ13ኛ ግዜ ነው ።

 በባዛርና አውደ ርእዩ ከ200 በላይ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው በመሳተፍ ላይ ናቸው ብለዋል ። 

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ለ1ሺህ 21 ኢንተርፕራይዞች ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል።

 ለኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስሩ የተፈጠረው ከኢንዱስትሪዎች፣ አገልግሎት ሰጭና ከሌሎች ተቋማትጋር መሆኑን ጠቅሰዋል።

 ከባዛርና ኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን 1ሺህ 21 ኢንተርፕራይዞችን በመጭው እሁድ ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የማሸጋገርና እውቅና የመስጠት መርሀ ግብር እንደሚከናወን አመላክተዋል።

ዘርፉ ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠርና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማሳካት አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። 

"ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርት በመግዛት የኢንተርፕራይዞች አቅም እንዲጠናከር ብሎም የገቢ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንዲቻል የድርሻችንን መውጣት አለብን"  ሲሉ አስገንዝበዋል ።

 የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው "በግብርና ዘርፍ የተገኘውን ድል በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት መድገም አለብን" ብለዋል ።

 ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከተመረቱ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች 41 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል። 

"ዘንድሮ ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት የተሻገሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንቨስትመንት ሲገቡ ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል ። 

"የፈጠራ ሃሳቦች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ሳይሰላቹ አዳዲስ ቴክኖሎጂ በምርምር የማውጣት ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው" ያሉት ደግሞ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ዶከተር ባይሳ በዳዳ ናቸው ።

 በተለይ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች በአንድ ማዕከል ተገቢውን የፈጠራ ስራ ማበልጸጊያ ማዕከልና የአቅም ማሻሻያ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ እረገድ የቡራዩ ማዕከል እንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል ። 

ኢንተርፕራይዞች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ በየደረጃው እንዲኖርና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው ዶክተር ባይሳ አስገንዝበዋል ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም