የቦረና የውሃ ፕሮጀክት ኔትወርክ ግንባታ በደረሰበት ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 የቦረና የውሃ ፕሮጀክት ኔትወርክ ግንባታ በደረሰበት ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የማህበረሰቡ የውሃ እጦትን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቦረና የውሃ ፕሮጀክት ኔትወርክ ግንባታን ከማከናወን ጎን ለጎን ለማህበረሰቡ ውሃ መቅረብ መቻሉን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ። 

በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የሚከሰተውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ ከ15 ዓመታት በፊት የተጀመረው የቦረና የውሃ ፕሮጀክት ኔትወርክ ግንባታ በጊዜው ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎች ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። 

የውሃ ፕሮጀክቱ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት እየተከናወነ ሲሆን ከሰሞኑ የከርስ ምድር ውሃው ከሚወጣበት እስከ 20 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ 

በሚኒስትሩ የተመራ የመንግስት የስራ ኋላፊዎች ቡድን የፕሮጀክቱን አፈጻጽም ተመልክቷል።  

ለአካባቢው መልክዓ ምድር የማይሆኑ ቱቦዎችን በአዲስ የመተካት ተግባራት በማከናወን ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ሳይጠበቅ ከከርሰ ምድር ውሃ መውጫ ቦታ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ አካባቢዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። 

በቦረና ዞን በግንባታ ላይ የሚገኙ 41 የውሃ ጉድጓዶችን በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዞኑን የውሃ እጥረት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከአጋር አካላት በተገኘ 12 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል። 

በዚህም በቀጣይ የውሃ ፕሮጀክቶችን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት በማጠናቀቅ የቦረና የውሃ እጥረት ችግር በዘላቂነት እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።  

ከቦረና የውሃ ፕሮጀክት ኔትወርክ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ለ15 ዓመታት ሲጠባበቁ የቆዩት ፕሮጀክት በተለይም የድርቅ አደጋ ክፉኛ እየፈተናቸው ባለበት በዚህ ወቅት አገልግሎት መጀመሩ አስደስቷቸዋል። 

ለሰው እና ለእንሰሳት ውሃ ፍለጋ ከአንድ ቀን በላይ የሚያደርጉት ጉዞ እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል። 

መንግስት በቦረና ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ አደጋ ከሰብዓዊ ድጋፎች አቅርቦት ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም