የዐድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋነኛ መሰረትና የነፃነት ድል የተረጋገጠበት ታላቅ በዓል ነው-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የዐድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋነኛ መሰረትና የነፃነት ድል የተረጋገጠበት ታላቅ በዓል ነው-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 23/2015 የዐድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋነኛ መሰረትና የነፃነት ድል የተረጋገጠበት ታላቅ በዓል መሆኑን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።
የዘንድሮው 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የመከላከያና የፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የሰራዊት አባላትና ሌሎችም ታዳሚዎች በተገኙበት በወታደራዊ ትርኢት ታጅቦ በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የዐድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋነኛ መሰረትና የነፃነት ድል የተረጋገጠበት ታላቅ የድል በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣን ጠላት ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር በመንቀሳቀስ በመስዋእትነት ድል ያደረጉበት የነፃነት ቀን መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዓድዋን ድል ዓለም ባደነቀው ልክ ማክበር አለብን ያሉት ፕሬዝዳንቷ ዘንድሮ አከባበሩን ከፍ በማድረግ ለነበረው ዝግጅትና አስደናቂ ወታደራዊ ትርኢት አመስግነዋል።
በመሆኑም የአድዋን ድል ስናከብር ከንትርክና ከሚከፋፍል እሳቤ በመውጣት ብሄራዊ ስሜትን በማጎልበት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።
በቀደምት አያቶች በክብር ተጠብቃ የቆየችውን አገር የአሁኑ ትውልድም ጠብቆ የማስቀጠል ሃላፊነትና ግዴታም ጭምር አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያዊያን በመተጋገዝ፣ በመተባበር፣ በመረዳዳትና በመግባባት የጋራ ችግሮችን ማሸነፍና የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ማለፍ ይገባል ብለዋል።