የአድዋ ድል የጀግንነታችን ጥግ፣ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፣ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የጀግንነታችን ጥግ፣ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፣ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ /ኢዜአ/ የካቲት 22/2015 የአድዋ ድል የጀግንነታችን ጥግ፣ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፣ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ 127ኛውን የአድዋ ድል በአል በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልእክት እንዳስታወቁት የአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያዊያን ለሐገራችን ሉዓላዊነትና ክብር ቅንጣት ያህል የማንደራደር ታላቅና ጀግና ህዝብ መሆናችንን ለዓለም ያስመሰከርንበት ነው"።
"ድሉ የአልደፈር ባይነታችን ወኔና ፅናታችን በተግባር የታየበት ብቻም ሳይሆን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የደመቀበት ገድል ነው " ሲሉም ተናግረዋል።
"የአድዋ ጦርነት ሲታሰብ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያስቆጣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ለአንድ አላማ ያስተሳሰረ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያዊነትን ያሳየ የጋራ የነፃነት ትግላችን ነው" ብለዋል።
በመላው አለም ያሉ ጥቁር ህዝቦች በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ ለደረሰባቸው የዘር መድልዎና የጭቆና ቀንበር ነፃ ለመውጣት ላደረጉት ትግል የአድዋ ድል የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንዳላበሳቸውም ገልፀዋል።
"የ127ኛውን የአድዋን ድል በዓል ስናከብር ኢትዮጵያውያን የጋራ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ክብርና የድል ፋና ወጊ በመሆኑ ለአባቶቻችን ተጋድሎ ታላቅ ክብር እየሰጠን መሆን ይገባዋል "ብለዋል።
"አባቶቻችን በጋራ አንድነታቸውና ህብረታቸው በአድዋ ወረራ ላይ ባደረጉት ተጋድሎ የጥቁር የአፍሪካውያንና የጥቁር ህዝቦች ኩራት እንደሆኑ ሁሉ ትውልዱ ድህነትን በጋራ ለማሸነፍና ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ከፍታ ለማሻገር ቁርጠኛ መሆን አለበት" ሲሉም አስገንዝበዋል።