የታላቁ ህዳሴ ግድብን ወደ ተሟላ ልማት ለማስገባት መላው ህዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

266

ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ወደ ተሟላ ልማት ለማስገባት እየተደረገ ላለው ጥረት መላው ህዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሄራዊ ምክር ቤት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለኢዜአ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎና ቁርጠኝነት እየተገነባ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

 ለግድቡ ግንባታ ህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍና ተሳትፎ ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም በተደረገ ሁሉን አቀፍ ጥረት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

 በተለይ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ የተከፈተው የህዳሴ ጉዞ ቁጥር ሁለት በሀገሪቱ 200 ከተሞችን በመድረስ ህዝቡን ማነሳሳት፣ መረጃ መስጠትና ሃብት ማሰባሰብን አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከየካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ክልል ከተሞች የሚደረገው ጉዞ መጀመሩን አስታውቀዋል።  

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አክለው የህዝቡን ድጋፍ በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በቦንድ ግዥ፣ በ8100፣ በፒን ሽያጭና በሌሎች የገቢ ማስባሰቢያ ዘዴዎች እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ ተሟላ ልማት ለማስገባት እየተደረገ ላለው ጥረት መላው ህዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

 “የህዳሴው ግድብ ግንባታን እንደጀመርነው ሁሉ ለማጠናቀቅ ህዝቡን ለማነሳሳት የህዳሴ ጉዞ ቁጥር ሁለት እንቅስቃሴ በተለያዩ ከተሞች መካሄድ ጀምሯል” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አምሃ ዓለሙ ናቸው።  

''ግድቡ ታሪካችን፣ ባህላችንና ቅርሳችን ነው'' ያሉት ስራ አስኪያጁ የጉዞው አላማም ህብረተሰቡን በማነሳሳትና ግንዛቤ በመፍጠር የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሃብት ለማሰባሰብ መሆኑን አመልክተዋል።

 የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ለገሰ ትዳሩ በበኩላቸው ግድቡ ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ የሚተርፍ ቋሚ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል። 

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያየ ጊዜ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዳኖሩ ገልጸው በቀጣይም ቦንድ የመግዛት እቅድ እንዳላቸው አመላክተዋል።

 ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተበባር ባዘጋጀው የህዳሴ ጉዞ ቁጥር ሁለት ንቅናቄ 200 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሃብት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም