የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአድዋ ድልን ቱሩፋቶች ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአድዋ ድልን ቱሩፋቶች ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአድዋ ድል በዓልን የህዝብን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ታሪኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞችና አመራሮች 127ተኛውን የአድዋ ድል በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ የአድዋ ድል በዓል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ በከፈሉት መሰዋዕትነት ነጻነትን ለትውልድ ያስረከቡበት ደማቅ ታሪክ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ አባቶች ከከፈሉት መሰዋዕትነት ብዙ የሚማረው ነገር አለ ያሉት አቶ ነጋሲ የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባውም አክለዋል።
በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በድሉ የታዩትን የአንድነትና የመተባበር ተግባራት ለትውልድ እንዲተላለፍ ዘወትር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ በበኩላቸው የአድዋ ድል በወቅቱ የነበሩት መሪዎችና መላው ህዝብ ተሳስሮ ለአንድ አላማ የቆመበት መሆኑን አስታውሰዋል።

ድሉ ብዙዎች በከፈሉት መሰዋዕትነት ሀገር ያጸኑበትና ሉዓላዊነቷ የተከበረች ሀገር ለትውልድ ያስተላለፉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቀው የመጡ ጣሊያኖች በኢትዮጵያውያን መሸነፋቸው ኢትዮጵያውያን የስልጣኔ፣የጠንካራ ስነ-ልቦና እና የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።
127ኛውን የአድዋን የድል በዓል አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የተቋሙ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።