"40 ከሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፤ ቀሪዎቹም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበናል"-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
"40 ከሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፤ ቀሪዎቹም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበናል"-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2015 (ኢዜአ) 40 ከሚሆኑ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ የደረሰው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቀሪዎቹም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በሀገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ 53 ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከአብዛኞቹ ጋር በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ከደረሱ ወደ 40 ገዳማ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ለመፈራረም እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሲቋቋም በኮሚሽነሮች ገለልተኛነት እና በምክክር ሂደቱ አካታችነት ላይ ጥርጣሬ አለን ያሉ የተወሰኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄዎች ሲያነሱ እንደነበር አስታውሰዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራዎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱ በመሆናቸው ኮሚሽኑ በኢ-መደበኛነት ከተነጋገራቸው በስተቀር ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር እስካሁን መግባባት ወይም ስምምነት ላይ እንዳልደረሰ ገልጸዋል።
ያም ሆኖ አሁንም ኮሚሽኑ መግባባት ላይ ያልደረሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ኮሚሽኑ እንዲመጡና በአጋርነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ ከሁሉም ወገን ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልግ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ጥያቄዎቻቸውን ይዘው በትብበር ለመስራት የማይፈልጉ አካላት በአቋማቸው ቢቀጥሉም ኮሚሽኑ ስራዎችን ከመከወን እንደማይገታ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሮች ተሹመውለት ስራ ከጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ዕቅዶቹ ቀነ-ገደብ ባይጠብቅም የፊታችን ግንቦት ውይይት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ለዚህም በቀጣይ ሳምንታት በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳድሮች ዋና ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ቅርንጫፎች እንደሚከፍት ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ከዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት ጋር ከተደረጉ ስምምነቶች በተጨማሪ ከእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ጋርም ስምምነቶች እንደሚደረጉ ገልፀው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው የሰው ሃይል፣ የፌዴራል ተቋም መሆናቸው እና ወጭ ቅነሳ ረገድ ያላቸው ሚናን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለቅርንጫፎች ቢሮነት እንደተመረጡ አስረድተዋል።
"ኮሚሽኑ ከተደራሽነትና በህብረተሰቡ ዘንድ ከተሰጠው ትልቅ ተስፋና ግምት አኳያ ስራዎቹ አልዘገዩም ወይ" በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፤ ኮሚሽኑ እስካሁን በውስብስብ ሂደቶች እንዳለፈ ገልጸዋል።
ከሰው ሃይል ማሟላት፣ ከህግ ማዕቀፍና ሌሎች ውስጣዊ ስራዎች ብዛት ባሻገር ሀገራዊ የሰላም ችግሮችና በየጊዜው የሚፈጠሩ አጀንዳዎች ኮሚሽኑ ስራዎቹን በጊዜው እንዳይከወን የራሳቸው አሉታዊ ተዕጽኖ እንደነበራቸው አንስተዋል።
ከሰሞኑም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ተቋማት ተወካዮች ጋር ባደረገው ውይይትም የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
አጀንዳዎች ልየታ ተጠናቆ የፊታችን ግንቦት ወር ውይይት እንደሚጀመር ገልፀው፤ ይህ ዕቅድ ክረምት ሳይገባ እንዲከናወን እንጂ ለቀጣይ በጀት ዓመት እንዲተላለፍ አንፈቅድም ነው ያሉት።
የውይይት ሂደቱ አሳታፊነትም ከአርሶ አደር እስክ አርብቶ አደር ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የስራዎቹን ተደራሽነት ለማሳደግም በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚሰሩ 70 ማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር በጋራ ለመስራት ውይይት ስለማድረጉ ተናግረዋል።