በባሌ ዞን ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማጎልበት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ተባለ

84
ጎባ  መስከረም 26/2011 በባሌ ዞን መስህቦችን በማስተዋወቅና በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተጠየቀ። ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን “ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ለቱሪዝም ልማት ! “ በሚል መሪ ቃል ትናንት በዞን ደረጃ በደሎ መና ወረዳ ተከብሯል፡፡ የባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደላ ኡዶ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት የቱሪዝም መሰህቦችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማጎለበት እየተሰራ ነው ፡፡ ኃላፊው እንዳሉት የባሌ ዞን የብዙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ እየተገኘ የሚገኘው ገቢ አነሰተኛ ነው ፡፡ "ባለፈው ዓመት የመስህብ ስፍራዎቹን ከጎበኙ 6ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ከ700 ሺህ ብር የማይበልጥ ገቢ መገኘቱ በዘርፉ ብዙ ስራ መስራት እንደሚጠብቅ ትልቅ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡ በመስህብ ስፍራዎቹ አካባቢ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት እጥረቶች፤ መስህቦቹን በሚገባ አለማስተዋወቅ ከተስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱም አመልክተዋል፡፡ የቱሪዝም ቀን መከበሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የቱርስት መዳረሻዎችን በማወቅ በዘርፉ ያለቸውን ተሳትፎና ልምድ ለማሳደግ  ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አቶ ታደለ ተናግረዋል ፡፡ በመስህብ ስፈራዎች አካባቢ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና አማራጮችን በመለየት መስህቦቹን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ከተሳተፉ መካከል ከጊኒር ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የመጣችው ወይዘሮ አሽረቃ ከዲር እንደገለጸችው “ በዓሉ በየዓመቱ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ መከበሩ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ” ይረዳል፡፡ መንግስት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት እንደሚደግፉም ተናግረዋል፡፡ "በዓሉ በቱሪስት መስህቦቹ አካባቢ መከበሩ በስፍራዎቹ አካባቢ የባህልና እደጥበብ ውጤቶችን በማዘጋጀት በኢኮ- ቱሪዝም ዘርፍ ተደራጅተው እየሰሩ የሚገኙ ሰዎችን ለማበረታታት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል" ያሉት ደግሞ ከጎባ ወረዳ በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፈው አቶ ሀሰን መሐመድ ናቸው፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ተሳትፈው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካል የሆነውን የሰናቴ አምባና የሀረና ጥቅጥቅ ደንን በመጎብኘታቸው ደሰተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባሌ ዞን  በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም/ ዩኔስኮ / በጊዜያዊ መዝገብ ላይ የሰፈሩትን የድሬ ሼህ ሁሴን፣ ሶፍ ኡመር ዋሻና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መገኛ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ከሁሉም ወረዳ የቱሪዝም ሴክተር መስሪያቤቶችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በወረዳው የሚገኙ የቱርስት መስህቦችን መጎብኘታቸው ታውቋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም