የእሁድ ገበያን መዳረሻና የምርት አቅርቦቱን በማስፋት አገልግሎት እየተሰጠ ነው- የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
የእሁድ ገበያን መዳረሻና የምርት አቅርቦቱን በማስፋት አገልግሎት እየተሰጠ ነው- የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 21/2015 በአዲስ አበባ ከተማ የእሁድ ገበያ መዳረሻዎችና የምርት አቅርቦቱን በማስፋት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለጸ።
ኤጀንሲው በመዲናዋ በሸማች ማኅበራት ሱቆች ከሚደረገው የሸቀጦች ግብይት በተጨማሪ በእሁድ ገበያ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ማድረጉ ይታወቃል።
የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጥላሁን ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የእሁድ ገበያ ከተጀመረ ጥቂት ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል።

በ5 ክፍለ ከተማና የገበያ መዳረሻዎች ሥራውን የጀመረው ገበያው በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ137 በላይ የገበያ መዳረሻዎችን እንደሚሸፍን አመልክተው በተመጣጣኝ ዋጋ በርካታ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረቡበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግብይቱ ቅዳሜን እንዲጨምር ለማድረግም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምርቶቻቸውን ለሸማች ይዘው የቀረቡት አቶ ዓለሙ ጸጋዬ ከዚህ በፊት የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማህበራቱ ሱቆች ብቻ ያቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ ።
የእሁድ ገበያ በመጀመሩ ደግሞ ነዋሪው ምርቶቹን በስፋት እንዲያገኝና በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ጋር እንዲገናኝ ከማድረጉ ባለፈ ገበያውንም የማረጋጋትና የማስፋት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በገበያው እየተሳተፉ ያገኘናቸው ሸማቾች በበኩላቸው የገበያ መዳረሻዎች መስፋታቸውና የምርት አይነቱ እንዲጨምር በመደረጉ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ዘላለም ሞገስ ’በአቅርቦቱ እኔ በብዛት ተጠቃሚ ነኝ ሲሉ ገልጸው በአንዳንድ ምርቶች ላይ ግን ዋጋ ይበልጥ የመቀነስ ስራ እንዲከናወን ጠይቀዋል።
በመዲናዋ 11 የሸማች ዩኒየኖችና ከ150 በላይ የሚሆኑ መሰረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየሰሩ ይገኛሉ።