በተቋማቱ ያለመናበብ ‘ክላሲ’ ውኃ ፋብሪካ ያለአግባብ ታሽጓል – ቅሬታ አቅራቢ

710

አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 በላያ ኢንዱስትሪያል ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚያመርተው ‘ክላሲ’ የታሸገ ውኃ “ምንም በማላውቀውና ትክክኛ ባልሆነ መንገድ ፋብሪካዬ ታሽጓል፣ ምርቱም ትክክለኛ ስለመሆኑም የተለያዩ ማስረጃዎች አሉኝ” ሲል ቅሬታ አቀረበ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ንግድ ሚኒስቴር ”ክላሲ የታሸገ ውኃ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ታግዷል” ሲል ይፋ አድርጓል።

ኢዜአም የተላከውን መግለጫ መነሻ በማድረግ መስከረም 15 ቀን ፋብሪካው ወደሚገኝበት ሱሉልታ አካባቢ አቅንቶ ፋብሪካው በር ላይ ”ከኢትዮጵያ አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች በታች በመሆኑ ታሽጓል” ተብሎ ስራ ማቆሙን አረጋግጧል።

ንግድ ሚኒስቴር ጉዳዩን መስከረም 10 ቀን ይፋ ባደረገ ከሁለት ቀን በኋላ ለተለያዩ አካላት ስልክ በመደወል ስለችግሩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ጥረት ብናደርገም ወዲያውኑ ምላሽ የሚሰጥ አልተገኘም።

ፋብሪካው እስከ መስከረም 14 ቀን ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በሙሉ አቅሙ ስራ ላይ እንደነበረ የፋብሪካው ባለቤት አቶ ዳኜ የስጋትም ይናገራሉ።

ፋብሪካው ከመዘጋቱ በፊት ለ350 ሰራተኞች በወር አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ደመወዝ የሚከፍለውና በዓመት ወደ 15 ሚሊዮን ብር በመገበር ስራውን ያከናውን ነበር።

የፋብሪካው ባለቤት አቶ ዳኜ የክላሲ ውሃን በተመለከተ ከመንግስት ተቋማት አስፈላጊውን የኢትዮጵያ ደረጃን አሟልቶ ስለ መስራቱ ማረጋገጫ እንዳላቸው ይገልጻሉ፤ ማስረጃቸውንም ያሳያሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በማያውቁትና ትክክለኝነት በጎደለው መልኩ ድርጅቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ተደርጓል።

 የፋብሪካው የጥራት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ንጉሴ ካሳ እንደሚሉት፤ የኢትጵያ ተስማሚነት ምዝና ድርጅት በ2010 ዓ.ም ብቻ በጥቅምት፣ በመጋቢት፣ በሃምሌና በጳጉሜ ላይ ባደረገው ምዝና ውኃው አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ያሟላ መሆኑ አረጋግጦ ማስረጃ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የመድሃኒት፣ የምግብ፣ ጤና እንክብካቤና ቁጥጥር ባለስልጣን ነሃሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በሰጠው ማረጋገጫ “ውኃው ችግር እንደሌለባት ያሳያል” ብለዋል።

ኢዜአም መመልከት እንደቻለው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጳጉሜን 1 ፣ መጋቢት 5፣ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በጻፈው የተለያዩ ደብዳቤዎች ምርቱ አስገዳጅ ደረጃን ያሟላ መሆኑን ያረጋግጣል። የኢትዮጵያ የመድሃኒት፣ የምግብ፣ ጤና እንክብካቤና ቁጥጥር ባለስልጣንም በተመሳሳይ ነሓሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም የጻፈውን የማረጋገጫ ደብዳቤ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ተስማሚኒት ምዘና ድርጅት በበኩሉ ክላሲ ውኃ ድርጅቱ ባደረገው የተለያዩ ፍትሻዎችን መነሻ በማድረግ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ በማሟላቱ ማስረጃዎቹን መስጠቱን አምኗል።

የምርት ጥራትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተሩ ጋሻው ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ ድርጅቱ የውኃ አምራቹ ኩባኒያ የምርት ሂደቱ ትክክለኛ መሆኑ በተደረገው ክትትል ታውቋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚኒት ምዘና ድርጅት 65 ውኃ አሽገው የሚሸጡ ድርጅቶች “የምርት ጥራት ሂደታቸውን ፍተሻ እያደረገ እየተከታተለ ይገኛል ነው” ያሉት።

ይህ ሆኖ ሳለ የንግድ ሚኒስቴር ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ከገቢያ የወሰደውን ናሙና መነሻ ማድረጉን ይገልጻል። ከዚህ ተነስቶም ከስድስት ወር በኋላ ውኃው በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ ስለተገኘ መታገዱን አስቷውቋል።

ኢዜአ ከንግድ ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ቢጠይቅም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ቀደም ብለው ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት የተለየ ማብራሪያ እንደማይሰጡ ተናግረው እርሱን እንድንጠቀም ገልጸውልናል።

የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ መስከረም 10 ቀን ለኢቲቪ ‘ሚኒስቴሩ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከድርጀቱና ከገቢያም በወስደው ናሙና መሰረት መስፈርቱን ያላሟል መሆኑ ተረጋግጧል’ ሲል ተናግረዋል።

ሆኖም ንግድ ሚኒስቴር ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ ተስማሚኒት ምዘና ድርጅትና የኢትዮጵያ የመድሃኒት፣ የምግብ፣ ጤና እንክብካቤና ቁጥጥርና አስተዳደር ባለስልጣን ያደረጉት ክትትል ይህን አያመለክትም።

መረዳት የሚቻለው አንድ የምርት ሂደቱ በትክክለኛው መንገድ ውስጥ ያለፈ ከሆነ ምርቱ በገበያም ላይ ተመሳሳይ “የጥራት ደረጃ ይኖረዋል” ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ሆኖ ሳለ ተጨማሪ ምርመራ ሳይደረግ ከስድስት ወር በፊት የተወሰደ ናሙናን መሰረት አድርጎ ይህን እርምጃ መውሰዱ ትክክል አይደልም ይላሉ የክላሲ ውኃ የምርት ጥራት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ንጉሴ ካሳ።

ውኃው የጤና ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ እንኳን ቢሆን በስድስት ወር ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ይህን ሁሉ ጊዜ መጠበቅም ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

ፋብሪካው 2009 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ የምርት ችግር አለበት ተብሎ ታሽጎ የነበረ ሲሆን ዳግም ‘የውዴታ ግዴታ ውል ተፈርሞ’ ወድ ስራ እንዲገባ መደረጉን ያስታውሳሉ።

በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የፋብሪካው ሰራተኞች ተበትነዋል፣ መንግስትም ድርጅቱ የሚያገኘውን ዓመታዊ ግብር ያጣል ማለት ነው።