የከተሞችን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወነው ስራ አበረታች ለውጥ እየመጣ ነው

ድሬደዋ ፤ የካቲት 20 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የሀገሪቱን ከተሞች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በተከናወነው ስራ አበረታች ለውጥ እየመጣ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃግብር /ዩ.አይ.አይ.ዲ.ፒ./ የስራ አፈፃፀምን የሚገመግም ሀገር አቀፍ ጉባኤ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤውን ያስጀመሩት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ በመንግስት ፣ በአለም ባንክ ድጋፍና ብድር ሁለት ቢሊዮን በሚጠጋ ዶላር በሶስት ምዕራፎች በ180 ከተሞች የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ስራዎች መሠረታዊ ለውጥ እያስገኙ ነው።

በተለይ በሶስተኛው ምዕራፍ በ859 ሚሊዮን ዶላር በ117 ከተሞች በመተግበር ላይ የሚገኘው የከተሞች ተቋማዊ ና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃግብር የከተሞቹን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብት በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

"የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በተለይ ወጣቶችና ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ አድርገዋል ፤ የከተሞችን ገፅታ ለውጠዋል ፤የከተሞችን ገቢ አሳድገዋል ፤የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጡን አሻሽለዋል" ብለዋል።

እነዚህ ተጨባጭ ለውጦች ይበልጥ ለማሳደግ ከተሞች ከፍተኛ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መሠረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ማስፋፋትና የመሠረተ ልማት ሀብት አስተዳደርን ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል ።

በተጨማሪም ከተሞች የራሳቸውን ገቢ እንዲያሻሽሉና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ከተሞችን መፍጠር ላይ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።

የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ወደ አገልግሎት በማስገባት የከተሞችን ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንዲሁም የአደረጃጀትና የአሠራር ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጀመረው ጉባኤ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ በማስቀመጥና የተሻሉ ተሞክሮዎች በመለዋወጥ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው፤ ባለፉት ሶስት የመርሃግብሩ ሂደት የተተገበሩ የዘመናዊ ቄራ፣ የጎርፍ መከላከያ ግንቦች፣ ሼዶች፣ መንገዶች፣ የመንገድ ላይ መብራቶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ድሬዳዋን ምቹ የስራና የመኖሪያ ስፍራ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል ብለዋል ።

የስራ ዕድል በመፍጠር፣የከተማዋን ማህበራዊና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎችን እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በተቀናጀ መንገድ የተሻለ ስራ ለማከናወን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የፌደራል ፣የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ኢዜአ ከድሬዳዋ ዘግቧል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም